Fana: At a Speed of Life!

ከ28 ዓመታት በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫ ያለፉ ብሔራዊ ቡድኖች…

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከ28 ዓመታት ጥበቃ በኋላ ወደ ትልቁ መድረክ የዓለም ዋንጫ ሦስት ብሔራዊ ቡድኖች አልፈዋል፡፡

ኖርዌይ፣ ስኮትላንድ እና ኦስትሪያ ከ28 ዓመታት ጥበቃ በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫ ያለፉ ሀገራት ናቸው፡፡

ኖርዌይ ለመጨረሻ ጊዜ በዓለም ዋንጫ የተሳተፈችው በፈረንጆቹ 1998 በፈረንሳይ አስተናጋጅነት በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ነበር፡፡

የኖርዌይ ብሔራዊ ቡድንን ወደ ዓለም ዋንጫ ካሳለፉ ወሳኝ ተጫዋቾች መካከል ቀዳሚ የሆነውና አሁን 25 ዓመቱ ላይ የሚገኘው ኤርሊንግ ብራውት ሃላንድ÷ ኖርዌይ ለመጨረሻ ጊዜ በዚህ መድረክ ስትሳተፍ አልተወለደም ነበር፡፡

5 ሚሊየን 640 ሺህ ገደማ ሕዝብ ያላት ኖርዌይ ከበርካታ ዓመታት ጥበቃ በኋላ በታሪኳ አራተኛ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ትኬቷን መቁረጥ ችላለች፡፡

የፊት መስመር ተጫዋች የሆነው ሃላንድ ባደረጋቸው ስምንት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች 16 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን÷ በ2026 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ቀዳሚው ነው፡፡

ሃላንድ ሀገሩን ከቡድን አጋሮቹ ጋር በመሆን ወደ ዓለም ዋንጫ በመመለስ የራሱን ትልቅ ታሪክ በኖርዌይ ብሔራዊ ቡድን ፅፏል፡፡

ለቢቢሲ አስተያየቱን የሰጠው ኖርዌያዊው ጋዜጠኛ ላርስ ሲቨርስተን ሃላንድ ድንቅ ኮከብ ነው፤ እሱ የምንጊዜም ታላቁ ተጫዋች ነው በማለት አሞካሽቶታል፡፡

ጋዜጠኛ ላርስ ሲቨርስተን ከሃላንድ በተጨማሪ አሌክሳንደር ሶርሎዝ እና ማርቲን ኦዴጋርድ ለኖርዌይ ወደ ዓለም ዋንጫ መመለስ ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን አብራርቷል፡፡

ኦዴጋርድ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ 7 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ሲያቀብል ሶርሎዝ በበኩሉ አምስት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡

ሌላኛዋ ከ28 ዓመታት በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫ የተመለሰችው ሀገር ስኮትላንድ ናት፡፡

ድራማዊ ምሽት በነበረው የምድብ የመጨረሻ ጨዋታ ስኮትላንድ ዴንማርክን በማሸነፍ ነው የ2026 የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋን ያረጋገጠችው፡፡

ስኮት ማክቶሚናይ በጨዋታው ለሀገሩ ድንቅ የመቀስ ምት ግብ ያስቆጠረ ሲሆን÷ ስኮትላንድ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫ እንድትመለስ ትልቁን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡

ስኮትላንድ ምድቧን በ13 ነጥብ በበላይነት በማጠናቀቅ ነው ከ28 ዓመታት በኋላ ወደ ትልቁ መድረክ የተመለሰችው፡፡

በማንቼስተር ዩናይትድ የቀድሞ አሰልጣኝ ራልፍ ራኚክ የምትመራው ኦስትሪያ ከ28 ዓመታት በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫው የተመለሰች ሌላኛዋ ሀገር ናት፡፡

ኦስትሪያ በ19 ነጥብ ምድቧን በበላይነት በማጠናቀቅ ለ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ትኬቷን ከ28 ዓመታት በኋላ መቁረጥ ችላለች፡፡

በወንድማገኝ ፀጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.