Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ ቴሌኮም 3ኛውን ፈጣን የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያ ሥራ አስጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስገነባውንና ሦስተኛውን ፈጣን የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያ ሥራ አስጀምሯል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በዚህ ወቅት÷ ጣቢያው በአንድ ጊዜ እስከ 16 ተሽከርካሪዎችን የማስተናገድ አቅም እንዳለውና ይህም ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ቀደም ሲል በኢትዮ ቴሌኮም የተገነቡ ሁለት ጣቢያዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ በአንድ ጊዜ ለ48 የኤሌክትሪክ መኪኖች አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አቅም መፈጠሩን አብራርተዋል፡፡

አገልግሎት እየሰጡ በቆዩት የመጀመሪያዎቹ ሁለት የቻርጅ ጣቢያዎች ከ165 ሺህ በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ይህም ከ6 ሚሊየን በላይ ኪሎግራም ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ወደ ከባቢ አየር እንዳይለቀቅ ለመከላከል ያስችላል ነው ያሉት።

በጣቢያዎቹ የተገጠሙት 16 እጅግ ፈጣን የኃይል መሙያዎች እያንዳንዳቸው በሰዓት እስከ 180 ኪሎዋት የሚደርስ የመሙላት አቅም እንዳላቸው ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አስረድተዋል።

አሽከርካሪዎች አገልግሎቱን በራሳቸው ማግኘት እና ክፍያቸውንም በቴሌብር ሱፐርአፕ መፈጸም እንደሚችሉ አንስተዋል።

ኩባንያው እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ መኪና ስነ ምህዳር በስማርት ቴክኖሎጂ ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ማሳየቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

በዛሬው ዕለት ስራውን የጀመረው በመዲናዋ ሰሚት ፍየል ቤት አካባቢ የተገነባው ቻርጅ ማድረጊያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተደገፈና እጅግ የላቀ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም ሲሆን÷ ከተሽከርካሪዎቹ ዓይነት ጋር ራሱን የሚያጣጥም እጅግ ፈጣን ቻርጀር የተገጠመለት መሆኑም ተገልጿል።

በሄኖክ ለሜ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.