Fana: At a Speed of Life!

የጉባ ብስራት ፕሮጀክቶች ሀገርን የማበልፀግ ርዕይን እውን የሚያደርጉ ናቸው – ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በጉባ ብስራቶች ይፋ ያደረገቻቸው ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ሀገርን የማበልፀግ ርዕይን እውን የሚያደርጉ ናቸው አሉ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)።

በአዲስ አበባ ከተማ ሁሉም ክፍለ ከተሞች “የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች” በሚል ሀሳብ ሕዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂደዋል።

በየካ ክፍለ ከተማ በተካሄደው ህዝባዊ ውይይት ላይ፥ በመዲናዋና በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶች የህዝብና የመንግስት ቅንጅት ውጤት መሆናቸው ተነስቷል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) ከተሞችን ለመለወጥ በሚደረገው ጥረት የነዋሪው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ በጉባ ብስራቶች ይፋ ያደረገቻቸው ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ሀገርን የማበልፀግ ርዕይን እውን ያደርጋሉ ነው ያሉት፡፡

በተመሳሳይ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በተካሄደው ሕዝባዊ የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የብልፅግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ አስተባባሪ ሚኒስትር መለስ ዓለሙ እንደገለጹት፥ ከኑሮ ውድነት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቅረፍ ሰው ተኮር ልማቶችና አምራችነት ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው ከመድረኩ የተገኙ ግብዓቶችን የቀጣይ ልማትና መልካም አስተዳደር እቅዶች አካል በማድረግ ሁለንተናዊ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የመደመር መንግሥት የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑም በመድረኩ ላይ ተነስቷል፡፡

በጉለሌ ክፍለ ከተማ በተካሄደው ውይይት ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ እና የፍትህ ሚኒስትር ወ/ሮ ሀና አርዓያስላሴ የኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ብልፅግና የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶችን ለማሳካት ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል በትብብር መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በልደታ ክፍለ ከተማ በተካሄደው ሕዝባዊ መድረክ ላይ እንዳሉት፥ መንግስት በሁሉም ዘርፍ የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡

በዚሁ መድረክ ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ እንደ ሀገር ብሎም በመዲናዋ የተገኙ ስኬቶች በህዝብ አብሮነትና ተሳትፎ የተመዘገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ መተባበርና አብሮ መቆም እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.