የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የብዝኃነታችንን ዐቅም የምናልቅበት ቀን ነው – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሕገ መንግሥታዊ ቃል ኪዳናችንን የምናድስበትና የብዝኃነታችንን ዐቅም የምናልቅበት ቀን ነው አለ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፡፡
አገልግሎቱ 20ኛውን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ የሚገለጽ ብዝኃነት ባለቤት ናት፡፡ የቋንቋ፣ የባህል፣ የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የፖለቲካዊ አመለካከት፣ የዕድሜ፣ የፆታ ብዝኃነቶቿ የሚያስጌጧት ድንቅና ቀደምት ሀገር ናት፡፡
ይህንን ብዝኃነቷን እንደ እሴት የምታዳብርበት፣ እሴቱን ወደ መፈጸም ዐቅም የምትለውጥበት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዐት ባለቤትም ናት፡፡ ለዚህም ነው የጋራ የቃል ኪዳን ሰነድ በሆነው ሕገ መንግሥታችን አንድ የጋራ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት በነፃ ፈቃዳችን የተስማማነው፡፡
ምንም እንኳን የሥርዐተ መንግሥት ታሪካችን በርካታ ሺህ ዓመታትን ቢያስቆጥርም ሕገ መንግሥታዊ ልምምዳችን ግን በበቂ ያልዳበረ፣ ከአንድ ክፍለ ዘመን ያልተሻገረ ነው፡፡ ለዚህም ነው የዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ግንባታ ሂደታችን በምንሻው ልክ ያልጎለበተው፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዐታችንን መሠረት ለማስያዝ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ስኬቶችም እየተመዘገቡ ይገኛሉ፡፡ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩና እንዲጠበቁ፣ የግልጽነትና ተጠያቂነት ሥርዐት እንዲጎለብት፣ ገለልተኛና ጠንካራ ሀገራዊ ተቋማት እንዲፈጠሩ፣ የሕዝቦች የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ መንግሥት በልዩ ትኩረት እየሠራ አስደማሚ ስኬቶችም እየተመዘገቡ ነው፡፡
በሕገ መንግሥታችን ዕውቅና ያገኙ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በአግባቡ እንዲከበሩና እንዲጠበቁ ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማት እየተገነቡ ነው፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲጎለብት ገለልተኛ የፍትሕ ሥርዐትን እውን ከማድረግ ባሻገር ብዝኃነትን የሚያስተናግድ ዓውድ ተፈጥሯል፡፡
ኢትዮጵያውያን ባህላቸውን፣ ትውፊታቸውን፣ ማንነታቸውን፣ መሻታቸውን የሚያስተዋውቁበት ሥርዐት በሕገ መንግሥታችን እውን የሆነበትን ኅዳር 29 ቀን በየዓመቱ በልዩ ልዩ ሁነቶች እያከበርን የእርስ በርስ ትውውቃችንን እያጠናከርንና የበለጠ አንድነታችን እያዳበርንበት እንገኛለን፡፡
በበዓሉ የብዝኃነታችንን ዐቅም አልቀን አሳይተናል፡፡ የሕዳሴ ግድባችንን እውን ለማድረግ የሚያስችል ገንዘብ ለማሰባሰብ የተጠቀምንበትም ይህንን በዓላችንን ነበር። በውጤቱም ሕዳሴን አሳክተን ብዝኃነታችን ዐቅማችን እንደሆነ አረጋግጠንበታል፡፡ የወል የድል ታሪክ አስመዝግበንበታል፡፡
ኢትዮጵያ ብዝኃነቷን የሚያስተናግድ ሥርዐት ዘርግታለች፡፡ ብዝኃነት ጌጧ እና ዐቅሟ መሆኑንም ተገንዝባለች፡፡ ለዚህም ነው ከለውጡ ማግሥት የኢትዮጵያ ጉዞ በብርሃን፣ መዳረሻዋም ብልጽግና ሆኖ እየታየ ያለው፡፡
በውስጥ ባንዳዎችና በሩቅ ባዕዳን ሴራ ልዩነታችን መለያያችን ሆኖ ለዘመናት ተቀንቅኗል፤ አብሮነታችን ሲፈታተንና ከስኬታችን ሲጎትትም ኖሯል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሕዝባችን ይህንን ተገንዝቧል፡፡ የኢትዮጵያ መሻት፣ ትልምና ብልጽግና በአብሮነት እንደሚረጋገጥ፤ አብሮነታችን በብዝኃነታችን እንደሚያጌጥ፤ ብዝኃነታችን ዐቅማችን መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ ዴሞክራሲያዊ መግባባት እና ሕገ መንግሥታዊነት ደግሞ መንገዶቻችን ናቸው፡፡
ለዚህም ነው “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልእክት የኢትዮጵያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን እያከበርን የምንገኘው፡፡
እንኳን ለ20ኛዉ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን አደረሳችሁ!
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት