የጋራ ቤታችንን መሰረቱ ሳይናጋ ለማኖር የጋራ ማንነት ሊኖረን ይገባል – አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር የጋራ ቤታችንን መሰረቱ ሳይናጋ ለማኖር የጋራ ማንነት ሊኖረን ይገባል አሉ።
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ በክልሉ ሆሳዕና ከተማ እየተከበረ ይገኛል።
በበዓሉ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ የብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
አፈ ጉባኤው በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የጋራ ቤታችን መሰረቱ ሳይናጋ ለማኖር የጋራ ማንነት ሊኖረን ይገባል ብለዋል።
ይህንንም ለማጽናት በብሔራዊነት ላይ የተመሰረተ አሰባሳቢ ትርክት መገንባት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል የሚከበረው እርስ በርስ ለመተዋወቅ፣ ባህላዊ እሴቶችንና ልምዶችን ለመለዋወጥ እና ህብረ ሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ለማጠናከር እንደሆነ ተናግረዋል።
እንዲሁም ለዘላቂ ሰላም፣ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ እና ለፈጣን እድገት ብሔር ብሔረሰቦች በጋራ እንዲቆሙ ማድረግ የበዓሉ መሰረታዊ እሳቤዎች እንደሆኑ አስረድተዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በዓሉ የአብሮነትን እሴት በማጠናከር፣ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደትን በማፋጠን፣ ሰላምን በሚያጸኑ፣ እኩልነትንና ወንድማማችነትን በሚያጎለብቱ፣ ዘላቂ ልማትንና ሁለተናዊ ብልጽግናን በሚያፋጥኑ ተግባራት ታጅቦ ሲከበር መቆየቱን አንስተዋል።
ዘንድሮ ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን በተመረቀበት፣ ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች በተበሰሩበት ማግስት፣ ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ ዝግጅት በተጠናቀቀበት እንዲሁም 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሚደረግበት ዋዜማ መከበሩ በዓሉን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
በዓሉ በህብረ ብሔራዊ አንድነት የደመቀ ማንነታችን ለዓለም የምናሳይበት፣ ሁሉም ማንነቶች እኩል የሚስተናገዱበት እውነተኛ የፌዴራል ስርዓት በመገንባት ሂደት አዲስ የታሪክ እጥፋት ላይ መሆናችንን የምናስገነዝብበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ከኩስምና ወደ ማንሰራራት የተሸጋገርንበት፣ ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ጽኑ መሰረት ላይ ለማቆም የማያወላውል እምነት የማይቀለበስ አቋም ያለን መሆኑን የምናረጋግጥበት፣ በጋራ የመልማት ቃል ኪዳናችንን የምናድስበት ቀን ላይ ሆነን የምናከብረው በዓል ነው ሲሉም አመልክተዋል።
መንግሥት ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ሁለተናዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ ብዝሃነትንና አንድነትን መሰረት በማድረግ ይተጋል ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ለዚህም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ህብረ ብሔራዊ አንድነት እና ዲሞክራሲያዊ መግባባት የማይነጣጡሉ መሆናቸውን ለማረጋጋጥና ለማጠናከርና እውነተኛ የፌዴራል ስርዓት መገንባት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
በሶስና አለማየሁ