Fana: At a Speed of Life!

በተመጣጣኝ ዋጋ ሸማችና አምራች የሚገናኙበት…

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የላፍቶ ቁጥር-2 ሁለገብ የገበያ ማዕከል ሸማችና አምራች በማገናኘት በመዲናዋ ገበያን በማረጋጋት ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

የገበያ ማዕከሉ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የጥራጥሬ እህሎች፣ የሰብል ምርቶች፣ በርበሬና ቅመማ ቅመም፣ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ጨምሮ ሸማቹ የሚፈልጋቸው ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ በአንድ ቦታ የሚገኙበት ነው፡፡

በዚህ ግዙፍ የገበያ ማዕከል ከሚቀርቡ ምርቶች በተጨማሪ ባንኮች፣ ወፍጮ ቤቶች፣ የታክሲ ተርሚናሎች፣ ካፍቴሪያና ሌሎችም አገልግሎቶች ይገኙበታል።

እነዚህ አገልግሎቶች የከተማዋ ነዋሪዎች የገዙትን እህል እዚያው በማዕከሉ ውስጥ አስፈጭተው መውሰድ እንደሚችሉም ነው የተገለጸው፡፡

ፋና ፖድካስት በገበያ ማዕከሉ ቅኝት ባደረገበት ወቅት የከተማ አስተዳደሩ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ እንዳሉት፥ መንግስት የገበያ ማዕከሉን ገንብቶ ለምርት አቅራቢዎችና ለነጋዴዎች እያቀረበ ይገኛል፡፡

በመሆኑም የሁሉም ምርቶች ዋጋ ከነጻ ገበያው 20 በመቶ እንደሚቀንስ ገልጸው፥ የገበያ ማዕከሉ መቋቋም ዋና ዓላማም የኑሮ ውድነቱን ማረጋጋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በከተማ ግብርና የተሳተፉ ነዋሪዎችም የእድሉ ተጠቃሚ ሆነው ምርታቸውን እንደሚያቀርቡ የገለጹት ኃላፊዋ፥ ይህም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሸማች ብቻ ሳይሆኑ አምራችም መሆናቸውን ያሳያል ነው ያሉት።

የገበያ ማዕከሉን ንጽህና ለመጠበቅ በአካባቢው የቆሻሻ ማስወገጃ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡

በሁለገብ የገበያ ማዕከሉ እንቁላል በ13 ብር፣ ዘይት በ1ሺህ 400 ብር፣ ጤፍ ከ8 ሺህ እስከ 12 ሺህ ብር ይሸጣል። ሌሎችም ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ይቀርባሉ።

በብርሃኑ አበራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.