Fana: At a Speed of Life!

ትውልዱን በሥነ ምግባር በማነጽ ለሙስና የማይበገር ዜጋ መፍጠር ይገባል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ታሕሳስ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ትውልዱን በሥነ ምግባር በማነጽ ለሙስና የማይበገር ዜጋ ለመፍጠር በትኩረት መስራት ያስፈልጋል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።

22ኛው ዓለም አቀፍ የጸረ ሙስና ቀን በዛሬው ዕለት በተለያዩ መርሐ ግብሮች እየተከበረ ነው፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የምናየው ሀገራዊ ለውጥ እና እድገት የተመዘገበው የመደመር መንግሥት መንግሥታዊ ሙስናን አምርሮ የሚጠየፍ በመሆኑ ነው።

ብሔራዊ የጸረ ሙስና ኮሚቴ በማቋቋም ስለጉዳዩ በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር እንዲሁም ዘላቂ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማመልከት የሚያስችሉ የንቅናቄ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት ሙስናን መከላከል የሚቻለው በሦስት መንገዶች ነው ብሎ እንደሚያምን አስረድተዋል፡፡

የመጀመሪያው ራሱ መንግሥት ከመንግሥታዊ ሙስና ራሱን ነጻ ማድረግ የሚል ሲሆን÷ ይህም ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ በመንግሥትነት ተደራጅቶ የሀገርንና የሕዝን ገንዘብ የመዝረፍ ልማድ ያስቆመ ነው ብለዋል።

በዚህ ረገድ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች እና የተመረጡ የሙያ ክፍሎች ሠራተኞች ሃብታቸውን እንዲያስመዘግቡ የሚያስገድድ አዋጅ መተግበሩን አስታውሰዋል።

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም መጀመሩን ጠቅሰው ÷ ይህም እንደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዓይነት አዳዲስ የአሠራር መንገዶች እንዲዘረጉና ግልጽነትና ተጠያቂነትን በመፍጠር ሙስናን መከላከል ማስቻሉን አመልክተዋል።

የትውልድን ሥነ ምግባር መገንባት እና ለሙስና የማይበገር ዜጋ መፍጠርም ሌላኛው መንገድ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በተጨማሪም የሙስና መከላከል ተግባር በሦስት “መ” ዎች እንደሚጠቃለል አስገንዝበዋል፡፡

1ኛው “መ” መገንባት ማለትም የትውልድን ሥነ ምግባር መገንባት ፤ 2ኛው “መ” መከላከል ይህም ተቋማዊ አሠራርን ማዘመን ሲሆን ÷ 3ኛው “መ” ደግሞ መከበር፣ ለሙስና ወንጀል ሕግ መከበር ሁሉም ቁርጠኛ መሆን አለበት የሚሉ እንደሆኑ አብራርተዋል።

በለይኩን አለም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.