Fana: At a Speed of Life!

በአፋር ክልል የተገኘው 1 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚደርስ ዕድሜ ያለው ቅሪተ አካል…

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፋር ክልል በጎና መካነ ቅርስ ስፍራ 1 ነጥብ 5 የሚደርስ እድሜ ያለው የራስ ቅል እና ፊት ተገኘ።

ግኝቱ የጎና ፕሮጀክት የምርምር ውጤት በሚል ርዕስ በኔቸር ኮሙኒኬሽን የታተመ ሲሆን÷ ኢትዮጵያ የሰው ልጅ ዘር መገኛ መሆኗን ያጠናከረ መሆኑ ተገልጿል።

በስፔን የሰው ዘር አመጣጥ ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪና ሳይንቲስት ስለሺ ሰማው (ዶ/ር)÷ ግኝቱ ዕድሜው 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዓመታት እንደሚደርስ መገመቱንና በምስራቅ አፍሪካ ከሚታወቁት ከሆሞ ኢሬክተስ ዝርያዎች ጋር ሲወዳደር የተሟላ ገፅታ እንዳለው ተናግረዋል።

በቅሬተ አካሉ የሰው ልጅ ዝርያ ግንድ የሆነው ሆሞ ኢሬክተስ ምንጩ አፍሪካ ስለመሆኑ ያረጋገጠ ነው ያሉት ስለሺ (ዶ/ር)÷ የጥናቱ ውጤት በቨርቹዋል ሪኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ታግዞ የፊት ገፅታ ምሉዕነት የታየበት ነው ብለዋል።

በአፍሪካ እስካሁን ከተገኙት ተቀራራቢ እድሜ ካላቸው ግኝቶች የመጀመሪያው የተሟላ የራስ ቅልና የፊት አጥንቶች ጥርሶቹን ጨምሮ ለማየት እንዳስቻላቸው አብራርተዋል፡፡

የተገኘው የራስ ቅል የፊት ቅርፅ ከ300 ሺህ ዓመታት በፊት የነበረ ዕድሜያቸው 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ዓመታት የሚገመቱና ለመጀመሪያ ጊዜ አፍሪካን ለቀው ወደ አውሮፓና እስያ ከፈለሱት የቅድመ ሰው ዝርያዎች የጭንቅላትና የፊት ገፅታ ጋር ተመሳሳይነት እንዳለውም አስረድተዋል።

ይህም የፈለሰው የቅድመ ሰው ዝርያ ከጊዜ በኋላ ከእስያ ወደ አፍሪካ ተመልሷል የሚለውን መላምት ውድቅ አድርጓል ብለዋል።

ሆሞ ኢሬክተስ በአፍሪካ ውስጥ በአዝጋሚ ለውጥ የአሁኑ የሰው ዘር ግንድ መሆኑንና ኢትዮጵያም የሰው ዘር መገኛ መሆኗን የሚያጠናክር ግኝት መሆኑን አንስተዋል።

ሆሞ ኢሬክተስ በመባል በሚታወቀው የቅድመ ሰው ዝርያ ጭንቅላትና ፊት በቨርቹዋል ዲጂታል ሪኮንስትራክሽን በሳይንቲስቶች መጠናቱንና ቀደምት የሰው ዝርያዎች ከአፍሪካ ወደ ተለያዩ አሕጉራት ያደረጉትን እንቅስቃሴና ኦልድዋን እና አሹሊያ በመባል በሚታወቁ የድንጋይ መሳሪያ መጠቀማቸውን በተመለከተ ግኝቱ አዲስ መረጃ ነው ብለዋል።

እነዚህ የድንጋይ መሳሪያዎች ከሆሞ ኢሬክተስ ጋር በአንድ ላይ መገኘታቸው በአርኪዎሎጂ ጥናት እምብዛም ያልተለመደ በመሆኑ የጎናውን ግኝት አስደናቂ እንደሚያደርገው አመልክተዋል።

የቨርቹዋል ሪኮንስትራክሽኑ ስራ ከዓመት በላይ ጊዜ እንደወሰደባቸው፣ የተገኘው የራስ ቅልና ፊት ከሌሎች ተመሳሳይ ዕድሜ ካላቸው የቅድመ ሰው ዝርያዎች የአንጎሉ መጠን አነስተኛ መሆኑን በጥናቱ ከ300 ሺህ ዓመታት በፊት ከነበሩ ሆሞ ሀቢሊስ በመባል ከሚታወቁት የቅድመ ሰው ዘር ዝርያ ጋር መመሳሰሉን ጠቅሰዋል፡፡

የጎና የፓሊዎአንትሮፖሎጂ ጥናት ፕሮጀክት ባለፉት 30 ዓመታት የምርምር ስራው በዓለም ጥንታዊና 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ዓመታት ያስቆጠሩ የድንጋይ መሳሪያዎችንና 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ዓመታት ያስቆጠረውን አርዲፒተከስ ራሚደስ የተባለውን ጥንታዊ የሰው ዘር ቅሪተ አካል በማግኘት በተለያዩ ዓለም አቀፍ የሳይንስ ጆርናሎች ላይ ማሳተሙን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን አስታውቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.