Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት የአፍሪካ-ሕንድ ግንኙነትን ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት የአፍሪካ-ሕንድ ግንኙነትን ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው አለ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፡፡

የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ታሪካዊ ጉብኝት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፥ ጉብኝቱ የሁለቱን ሀገራት የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑን አመልክቷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ በሕንድ የአፍሪካ ፖሊሲ ማዕቀፍ ውስጥ እየጨመረ የመጣውን የኢኮኖሚ ትስስር፣ የሁሉ አቀፍ ልማትና ስትራቴጂያዊ ትብብር፣ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የሚያጎላ እንደሆነ ገልጿል፡፡

አገልግሎቱ በመግለጫው የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጉብኝት ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር ዋነኛ ዲፕሎማሲያዊ ማዕከል መሆኗን የሚያረጋግጥ ነው ብሏል፡፡

ጉብኝቱ ከተለመደው የዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ባለፈ ሕንድ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ወደዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከርና የዓለም አቀፉን የደቡብ ድምጽ በጋራ ለማጉላት ያላት ፍላጎት መጨመሩን የሚያሳይ መሆኑንም አንስቷል፡፡

የአገልግሎቱ ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ኢትዮጵያና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት የአፍሪካ ሕንድ ግንኙነት ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው፡፡

ጉብኝቱ ኢትዮጵያ በሕንድ የአፍሪካ ፖሊሲ ማዕቀፍ ውስጥ ያላትን እየጨመረ የመጣውን የኢኮኖሚ ትስስር፣ የሁሉ አቀፍ ልማትና ስትራቴጂያዊ ትብብር፣ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጎላ ሲሆን፥ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር ዋንኛ ዲፕሎማሲያዊ ማዕከል መሆኗን ያረጋግጣል፡፡

በተጨማሪም ከተለመደው የዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ባለፈ ሕንድ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ወደዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከርና የዓለም አቀፉን የደቡብ ድምጽ በጋራ ለማጉላት ያላት ፍላጎት መጨመሩንም ያሳያል፡፡

ኢትዮጵያና ሕንድ በዘመናዊ ዲፕሎማሲ ከ1948 ዓ.ም ጀምሮ ግንኙነት የጀመሩ ቢሆንም ሀገራቱ ከ2 ሺህ ዓመት በላይ የዘለቀ ጥልቅ ታሪካዊ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት ስለመሆናቸው የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ ፡፡

ህንድ ኢትዮጵያን በአፍሪካ እና በሰፊው ዓለም መካከል እንደ ድልድይ አድርጋ በማስቀመጥ በአስተዳደር፣ በኢኮኖሚ ልማት፣ በንግድ ዘርፍ፣ በመሠረተ ልማትና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎችን በመደገፍ ዘላቂ ወዳጅነቷን አሳድጋለች፡፡

ሕንድ ከአፍሪካ በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሰላም ማስከበር እና በዘላቂ ልማት ባሉ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለማጠናከር ፍላጎቷ ከፍተኛ ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ወደ ኢትዮጵያ መምጣትም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የሀገራቸው ቁርጠኝነትን ከፍተኛ መሆኑን ያመላክታል፡፡

ህንድ የኢትዮጵያ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዲያድግና የጋራ ተጠቃሚነቷ እንዲረጋገጥ አጋዥ የሆነውን የብሪክስ አባል የመሆን ጥያቄ ከደገፉ አባል ሀገራት አንዷ ስትሆን በብሪክስ ማዕቀፍ ውስጥ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት መሻሻል በትብብር እየሰራች ትገኛለች።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር የሚያደርጉት ውይይትም በዋና ዋና ዘርፎች በተለይም በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በታዳሽ ኃይል ትብብር፣ በአቪዬሽንና በዲጂታል ሽግግሮች ዙሪያ ፍሬያማ ምክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡

ጉብኝቱ ከሁለትዮሽ ግንኙነቶች ባለፈ ኢትዮጵያ በበርካታ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ እያደገ የመጣውን ተደማጭነቷን የሚያሳይና ከዓለማችን 10 ግዙፉ ኢኮኖሚ ከገነቡ ሀገራት አንዷ የሆነቸው ሕንድ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ማዕከል አድርጋ መቀበሏን ማሳያ ነው፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ታሕሳስ 7/2018 ዓ.ም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.