ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ከሚገኙት የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ በውይይታችን በኢትዮጵያ እና ህንድ መካከል እያደገ የመጣውን ትብብርና የወል ቅድሚያዎች የሚያንፀባርቁ አዳዲስ የትብብር መስኮችን ቃኝተናል ብለዋል፡፡
ከውይይታቸው በኋላ ከሁለቱ ሀገራት ልዑካን ቡድኖች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማካሄዳቸውን ገልጸዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል በጉምሩክ የጋራ አስተዳደር ድጋፍ፣ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳታ ማዕከል ምስረታ የመግባቢያ ሥምምነቶች እና በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ላይ ያለንን ቁርጠኝነት በሚያጠናክረው የተባበሩት መንግሥታት የሰላም ማስከበር ሥራ የመግባቢያ ሥምምነት የፊርማ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተናል ነው ያሉት።
ህንድ የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ አጋር መሆኗን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የዛሬዎቹ ውይይቶችና ሥምምነቶች ለጋራ ጥቅም በተለያዩ ዘርፎች ያሉንን ትብብሮች ለማስፋት ያለንን የጋራ ቁርጠኛ አቋም ያሳያሉ ብለዋል፡፡