Fana: At a Speed of Life!

የጠ/ሚ ናሬንድራ ሞዲ ጉብኝት ኢትዮጵያ በባለብዙ ዋልታ ዓለም ግንባታ ላይ  ያላትን ቁልፍ ሚና ያረጋገጠ ነው – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የኢትዮጵያ ጉብኝት ኢትዮጵያ የባለብዙ ዋልታ ዓለም ግንባታ ውስጥ ያላትን ቁልፍ ሚና ያረጋገጠ ነው  አለ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት።

አገልግሎቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ እያደረጉት ያለውን ጉብኝት አስመልክቶ ያስተላለፈው መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

የኢትዮጵያና ሕንድ የስትራቴጂካዊ አጋርነት አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ!

ይህ ጉብኝት በብሔራዊ ቤተመንግሥት ከተደረገው ደማቅ አቀባበል ባለፈ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን “የተሰሚነት ቁመት” እና ሕንድ ለአፍሪካ ቀንድ የምትሰጠውን “ስትራቴጂካዊ ክብደት” የሚያሳይ ነው።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የዳታ ማዕከል(Data Centre) ለመመሥረት የተደረገው ስምምነት ለኢትዮጵያ እጅግ ከፍተኛ ትርጉም አለው።

ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ መረጃዎቿን በዘመናዊ መንገድ ለማደራጀትና የሳይበር ደህንነቷን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት ሕንድ በቴክኖሎጂ እንድታግዝ ያደርጋል።

ሕንድ በዲጂታል ዘርፍ ያላትን ዓለም አቀፍ የበላይነት ወደ ኢትዮጵያ ተቋማዊ ግንባታ በማምጣት፣ የሀገሪቱን ዲፕሎማሲያዊ ብቃት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል።

በጉምሩክ የጋራ አስተዳደር ድጋፍ ላይ የተደረገው ስምምነት የሁለቱን ሀገራት የንግድ ልውውጥ ለማቀላጠፍ የታለመ ነው።

ሕንድ 1.46 ቢሊየን ሕዝብ ያላት ሀገር እና ግዙፍ ገበያ ያላት እንደመሆኗ፣ ይህ ስምምነት የኢትዮጵያ ምርቶች ወደ ሕንድ ገበያ በቀላሉ እንዲገቡና በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ሕገ-ወጥ ንግድ ለመቆጣጠር የሚረዳ ሲሆን ይህ “የሀሳብ ገበያውን” ወደ “ተግባራዊ የንግድ ገበያ” የመለወጥ ስኬት ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የሰላም ማስከበር ሥራ የመግባቢያ ሥምምነት መፈረሙ የኢትዮጵያንና የሕንድን ዓለም አቀፋዊ ሚና ያጎላል።

ኢትዮጵያና ሕንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሰላም አስከባሪ ኃይል የሚያሰማሩ ሀገራት ሲሆኑ በዚህ ዘርፍ በጋራ ለመሥራት መፈራረማቸው፣ ሁለቱ ሀገራት ለዓለም ሰላምና ደህንነት ያላቸውን ቁርጠኝነት ከማሳየቱም በላይ፣ በአፍሪካ ቀንድና በሕንድ ውቅያኖስ አካባቢ ለሚታየው አለመረጋጋት በጋራ የመፍትሔ አካል ለመሆን ማቀዳቸውን ያሳያል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) “የወል ቅድሚያዎች” (Shared Priorities) ያሏቸው ነጥቦች፣ ሁለቱም ሀገራት በብሪክስ (BRICS+) እና በግሎባል ሳውዝ (Global South) አጀንዳዎች ላይ ያላቸውን ወጥ አቋም ያመላከተ ነው።

ጉብኝቱ ኢትዮጵያ የባለብዙ-ዋልታ (Multipolar) ዓለም ግንባታ ውስጥ ያላትን ቁልፍ ሚና ያረጋገጠ ሲሆን ሕንድ ኢትዮጵያን እንደ “ታማኝና የረጅም ጊዜ አጋር” መቁጠሯ፣ ለኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትና ለዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነት ትልቅ ስኬት ነው።

ይህ ታላቅ የሁለት የሰው ሃይል ሃያላን አገራት መካከል የተደረገው ውይይትና የፊርማ ሥነ-ሥርዓት ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚያስተላልፈው መልዕክት ግልጽ ነው፡-“ኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ አጋሮቿን እያበዛችና የዓለምን የቴክኖሎጂና የኃይል ማዕከል ከሆነችው ሕንድ ጋር ያላትን ቁርጠኝነት እያጸናች መሆኗን ያሳያል።”

ይህ ስኬት “የሀሳብ ገበያውን” በተግባራዊ ስምምነቶች የመራና የኢትዮጵያን “ግዙፍ ስብዕና” በዓለም መድረክ የሸጠ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.