የአማራ ክልል ፖሊስ አዲስ የሠራዊት ደምብ ልብስ አስተዋወቀ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ወቅቱን እና ጥራቱን የጠበቀ አዲስ የሠራዊት ደምብ ልብስ አስተዋውቋል።
የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) እንዳሉት ÷ ፖሊስ የሕዝብን ሰላምና ደህንነት የማስከበር ከባድ ኃላፊነቱን በብቃት ለመወጣት ተቋማዊ ቁመናውን ማዘመን አለበት።
የደምብ ልብሱ የፖሊስን ተቋማዊ ሪፎርምና ዝግጁነት የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመው÷ ለሠራዊቱ በዓይነት፣ በጥራትና በመጠን ተደራሽ እንዲሆን ተደርጎ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡
የደምብ ልብሱ ወቅቱን የዋጀና የፖሊስን ሙያዊ ክብር የሚያጎላ ነው ያሉት ኮሚሽነር ጀኔራሉ ÷ የሠራዊቱን ሁለንተናዊ ፍላጎት በማሟላት ረገድ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
አዲሱ የደምብ ልብስ የሠራዊቱን ሥነ ምግባርና ዝግጁነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግርና ለተግባራዊነቱም አመራሩ አስፈላጊውን ክትትል እንደሚያደርግ መጠቆሙን የክልሉ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል።