የፌደራል ተቋማት ዋነኛ ተልዕኮ የመደመር መንግሥትን እሳቤ ተግባራዊ ማድረግ ነው – ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌደራል ተቋማት ዋነኛ ተልዕኮ የመደመር መንግሥትን እሳቤ ተግባራዊ ማድረግ ነው አሉ የብልፅግና ፓርቲ የፌዴራል ተቋማት አደረጃጀት ፖለቲካ ዘርፍ ሰብሳቢ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፡፡
ለብልፅግና ፓርቲ የፌዴራል አደረጃጀት አመራሮች የውስጠ ፓርቲ ስርዓትን ለማጠናከር ያለመ ስልጠና በዛሬው ዕለት ተሰጥቷል።
ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ስልጠናው ማለም፣ ማቀድና መፈፀም የሚችል አመራር ለመፍጠር የሚያስችል ነው፡፡
የፌደራል ተቋማት ዋነኛ ተልዕኮ የመደመር መንግሥትን እሳቤ በተቋማቸው ተግባራዊ ማድረግ መሆኑን ገልጸው፥ የውስጠ ፓርቲ ስርዓትን መገንዘብ ተልዕኮን በውጤታማነት ለመፈጸም እንደሚያግዝ አስረድተዋል።
ይህንን ተልዕኮ ከግብ ለማድረስ በፓርቲው 2ኛ ጠቅላላ ጉባኤ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን መሰረት በማድረግ አደረጃጀቶችንና ተቋማዊ አሰራርን ለማጠናከር፣ ጠንካራ የአመራርና አባላት አመለካከትና ስነምግባር ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት።
በፌዴራል ተቋማት አደረጃጀት በዋናነት የጉባኤ አቅጣጫዎችንና የሩብ ዓመት አፈጻጸም ግምገማና የሱፐርቪዥን ግኝቶችን መነሻ በማድረግ የአቅም ግንባታ ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፥ የተለዩ ክፍተቶችን በስልጠና መሙላት አንዱ ግብ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በ2018 ዓ.ም ዕቅዶች ውስጥ የፖለቲካና የአጀረጃጀት ስራዎችን በማካተት ቀጣይ ትኩረት የሚጠይቁ ጉዳዮች ተለይተው እየተሰራባቸው ይገኛል ብለዋል፡፡
በስልጠናው ላይ የፌዴራል ተቋማት አመራሮችን ጨምሮ የክላስተሮችና የወረዳ አመራሮች እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የኢንስፔክሽንና ሥነምግባር አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።
በፓርቲው ውስጠ አሰራር ላይ ትኩረት ያደረጉ የስልጠና ሰነዶች በስልጠና መድረኩ ላይ ቀርበው ውይይት መደረጉን ፓርቲው ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡