ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 አካታች፣ ሉዓላዊ እና በግልጽ ዓላማ የሚመራ ነው – ሚሪያም አሊ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 አካታች ሉዓላዊ እና በግልጽ ዓላማ የሚመራ ስትራቴጂ ነው አሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የዲጂታል አማካሪ ሚሪያም አሊ።
ሚሪያም አሊ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ራዕይ፣ ዓላማ እና ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮችን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፤ ስትራቴጂው ብልጽግናን በመላው ኢትዮጵያ ማረጋገጥ የሚያስችል ነው።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ እንዴት ማስተዳደር፣ አገልግሎቶችን እንዴት መስጠት፣ ኢኮኖሚያችንን እንዴት ማሳደግ እንዳለብን እና እያንዳንዱን ግለሰብ የወደፊቷ ኢትዮጵያ እንዴት እንደምታሳትፍ የሚያስገነዝብ ነው ብለዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 መሰረት የጣለ እንደሆነ እና ዲጂታል 2030 ደግሞ ዲጂታል ኢኮኖሚውን በጥልቀት ማስፋፋት ዓላማው ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው÷ ራዕዩ ግልጽ እና ትልቅ ዓላማን ያነገበ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ዲጂታል አገልግሎቶችን ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ፣ ለዜጎቹ የሚተጋ መንግሥት፣ ሉዓላዊ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ሥርዓት፣ በመሰረቱ ኢትዮያዊ የሆነ ፈጠራ እና በአንድ ዘርፍ ያተኮረ ሳይሆን መላ ኢኮኖሚውን የሚለውጥ መሆኑን አብራርተዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ግልጽ ዓላማዎች ሰዎች እና ተቋማትን ማብቃት፣ ሁሉን አቀፍ ዲጂታል ተደራሽነትን ማረጋገጥ፣ አካታች የሆነ የኢኮኖሚ እድገትን ማፋጠን እና ኢትዮጵያን ዋና የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን ማድረግ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የሕዝብ ዲጂታል መሰረተ ልማት ለስትራቴጂው ዋነኛው ምሶሶ እና ቁልፍ የዲጂታል ኢኮኖሚን የሚያሳልጥ የማይታይ ሞተር ነው ያሉት አማካሪዋ÷ ይህም የፋይዳን፣ የዲጂታል ክፍያ እና የዳታ ልውውጥ ሥርዓቶችን የሚያካትት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ወደ አንድ ዲጂታል መንግሥት የሚያሸጋግርና አገልግሎቶችን ቀላል፣ ፈጣንና ተደራሽ እንዲሆኑ ያግዛል ነው ያሉት፡፡
የዲጂታል ሽግግሩን ተግባራዊ ለማድረግ ሕጎች፣ መረጃ፣ ክህሎት እና ታማኝነት ወሳኝ እንደሆኑ በማንሳት ግብርናን፣ ጤናን፣ ትምህርትን፣ ኢንዱስትሪን ጨምሮ ከተሞችን እና ክልሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የኃይል እና ኢንተርኔት ተደራሽነትን ማረጋገጥ፣ የተሻሻለ የሕዝብ አገልግሎት መዘርጋት፣ ዳታ ላይ የተመሰረቱ ውሳኔዎችን መስጠት፣ ለሳይበር መከላከል በቂ ዝግጁነትን ማሳካትና የኢትዮጵያን የዲጂታል መሪነት ማጎናጸፍ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ውጤቶች ናቸው፡፡
ዲጂታል ኢትዮጵያ በመንግሥት ጥረት ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል እና በአጋር አካላት ትብብር የሚተገበር እንደሆነም ሚሪያም አሊ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በዮናስ ጌትነት
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Facebook https://web.facebook.com/fanasport
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!