የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ልማት እውን ለማድረግ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ልማት እውን ለማድረግ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ማረጋገጥ ይገባል አሉ በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፡፡
አቶ አደም ፋራህ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት ÷ የኢትዮጵያን ሕብረ ብሄራዊ አንድነት ማረጋገጥ ካልተቻለ ዘላቂ ሰላምና ብልጽግናን እውን ማድረግ አይቻልም፡፡
ኢትዮጵያ ከግጭትና ድህነት አዙሪት መውጣት ያልቻለችው በተናጠል ማንነትና በሀገራዊ ማንነት መካከል ሚዛን መጠበቅ ስላልተቻለና ሁሉንም አቅሞች ለመጠቀም የሚያስችል አስተሳሳሪ ማንነት (ገዢ ትርክት) መፍጠር ባለመቻሉ ነው ብለዋል፡፡
ለችግሩ መፍትሄው ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን መገንባት ነው ያሉት አቶ አደም ÷ ይህም የሚሳካው የኢትዮጵያ ብዝሃነት መገለጫ የሆኑትን ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነት፣ ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ እንደጸጋ መቆጠር ሲችል ነው ብለዋል፡፡
ሕብረ ብሔራዊነት በወንድማማችነትና እህትማማችነት እሴት ላይ በተመሰረተ አኳኋን በብሔር ማንነትና በሀገራዊ ማንነት መካከል ሚዛን ለመጠበቅ የሚያስችል ጠንካራ ሀገራዊ አንድነት መፍጠር ማለት ነው ብለዋል፡፡
ስለሆነም ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ማረጋገጥ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲሁም ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡፡
ሕብረ ብሄራዊ አንድነትን ማረጋገጥ የሚቻለውም በዋናነት ሶስት ዋና ዋና ጉዳዮችን መከወን ሲቻል እንደሆነ ነው ያስረዱት፡፡
እነዚህም ብዝሃነትን የሚቀበል አስተሳሳሪ ትርክት መገንባት፣ ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥና አካታች የፖለቲካ ሥርዓት መገንባት ናቸው፡፡
የፖለቲካ ተሳትፎ እና አካታችነትን ለማረጋገጥ ብልጽግና ፓርቲ መመስረቱን አስታውሰው÷ ፓርቲው የአጋር ፓርቲ ሥርዓትን በማስቀረት አቃፊና አካታች መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል የፌዴራል ተቋማት ኢትዮጵያን እንዲመስሉ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ የመሰረተ ልማትና ሌሎች ሥራዎችን በሁሉም አካባቢዎች በፍትሃዊነት ለማዳረስ ትኩረት መደረጉን አብራርተዋል፡፡
ነጠላ ትርክትን በመታገል ገዢ ወይም ብሄራዊ ትርክት በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ እንዲሰርጽና የበላይነት እንዲይዝ በቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
በሁሉም ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ እውን የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና የዓድዋ ድል መታሰቢያ እንዲሁም የጋዝና አፈር ማዳበሪያ ፋብሪካዎች ብሔራዊ ትርክትን ለመገንባት ሚናቸው ጉልህ መሆኑን አውስተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Facebook https://web.facebook.com/fanasport
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!