Fana: At a Speed of Life!

“ፋይዳ” ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 መሳካት ያለው ሚና…

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፋይዳ መታወቂያ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን በስኬት ለማጠናቀቅ ጉልህ ሚና አለው አሉ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና አስተባባሪ ዮዳሔ አርአያሥላሴ።
አቶ ዮዳሔ ፋይዳ መታወቂያ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ መሳካት ያለውን ሚና አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በዚህም ፋይዳ መታወቂያ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 እና 2030 ስታራቴጂ ላይ እንደ ቁልፍ መሰረት የተቀመጠ ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ይህ የሆነበት ምክንያትም ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ከሚሰጠው ሁሉን አቀፍ አገልግሎት አንጻር ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
መታወቂያው ባዮሜትሪክ በመሆኑ ለእያንዳንዱ ግለሰብ የየራሱ መለያ የሚሰጥ ሲሆን÷ የግል መረጃዎችን ለመጠበቅና ለአገልግሎት ጥራት እንዲሁም ፍጥነት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ዲጂታል መታወቂያ ትክክለኛ የሥነ ሕዝብ መረጃ መሠረት በመሆን ለብሔራዊ ልማት እቅዶችና በጀት ምደባ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታልም ነው ያሉት።
ለስማርት መንግሥት ግንባታ ዲጂታል መታወቂያ አስፈላጊ ነው ያሉት አቶ ዮዳሔ ÷ ዜጎች የሚፈልጉትን ውል፣ ሰነድና የትኛውንም አገልግሎት ከስልካቸው የሚያገኙበትን ሥርዓት እንደሚዘረጋ ገልጸዋል።
የፌዴራል እና የክልል ተቋማት ተናበው በመስራት ትስስራቸውን ይበልጥ እንዲያጠናክሩ መሰረት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዋና አስተባባሪው 30 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ለዲጂታል መታወቂያ መመዝገባቸውን ጠቁመው ÷በመጪው ሰኔ ወር መጨረሻ 90 ሚሊየን ዜጎችን ለመመዝገብ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በሶስና አለማየሁ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.