Fana: At a Speed of Life!

የኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ፖሊሲ የዲጂታል ሥራ ፈጠራን የሚደግፍ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ፖሊሲ ከዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ጋር ተጣጣሚ በሆነ መልኩ የዲጂታል ሥራ ፈጠራንና ተወዳዳሪነትን የሚደግፍ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ በሁሉም መስክ የሥራ ፈጠራ ባህልን በማስረጽ ቀጣይነት ያለው እና ፈጣን ዕድገትን ዕውን ለማድረግ ኢንተርፕረነርሽፕ ቁልፍ መሳሪያ ነው ብለዋል።

የኢፌዲሪ ኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ረቂቅ ፖሊሲን በተመለከተ ከዲጂታል ካውንስል አባላት ጋር በዛሬው ዕለት በበይነ መረብ ውይይት መካሄዱን ገልጸዋል።

የኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ፖሊሲ በዋናነት ሁሉን አቀፍ እና አካታች ሀገራዊ የኢንተርፕረነርሽፕ ንቅናቄን የሚያቀጣጥል መሆኑን አብራርተዋል።

ይህም ከዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ጋር ተጣጣሚ በሆነ መልኩ የዲጂታል ሥራ ፈጠራንና ተወዳዳሪነትን የሚያበረታታና የሚደግፍ እንደሆነ ተናግረዋል።

የፖሊሲ ማዕቀፉ ችግር ፈች ማህበረሰብን ለመገንባት፣ የፈጠራ ባህልን ለመጎልበት፣ እሴትን ለመጨመር እንዲሁም ምቹ ስነምህዳርን ለመገንባት የሚያስችል የኢኮኖሚ ዕድገት ማዕቀፍ ነው ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የሀገራችንን የኢንተርፕረነርሽፕ ስነምህዳርና የስራ ፈጠራ ውጥኖችን አቅጣጫ በመስጠት የመምራት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል በማለት ገልጸዋል።

በተለይ የኢንተርፕረነርሽፕ ስነምህዳሩን ሊያሻሽሉ የሚችሉ የጋራ አመለካከቶችን፣ እምነቶችንንና ባህሪያትን ለማጎልበት በዕጅጉ የሚያግዝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ይህ የልማት ፖሊሲ የታለመለትን ውጤት እንዲያመጣ በፖሊሲው ትግበራ ወቅት የሚታዩ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችን በመለየት በየደረጃው ወጥና ጠንካራ የክትትል ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ከዲጂታል ካውንስሉ ጋር መግባባት ፈጥረናል ነው ያሉት።

በመጨረሻም በኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ጥልቅ ውይይት በማድረግ እና ግብዓቶችን በመጨመር የልማት ፖሊሲ ሰነዱ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ተልኮ እንዲፀድቅ ወስነናል ብለዋል በመልዕክታቸው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.