በምርምር በተገኘ ዝርያ የቡና ምርታማነትን በሄክታር 28 ኩንታል አድርሰናል – ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር)
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በምርምር በተገኘ ዝርያ የቡና ምርታማነትን በሄክታር 28 ኩንታል አድርሰናል አሉ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር)።
በ2017 በጀት ዓመት በቡና ምርት ለመጀመሪያ ጊዜ ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ መመዝገቡ ይታወሳል።
ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በዘርፉ ከፍተኛ የሆነ እመርታዊ ለውጦች እየተመዘገበ በመምጣቱ ባለፈው በጀት ዓመት 470 ሺህ ቶን ቡና በመላክ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል።
በዚህም የተመረጡ የዘር ዓይነቶችን ከመጠቀም ጀምሮ የቡና ጥራት እና ምርታማነትን የሚጨምሩ ስራዎች በቅንጅት በመሰራት ላይ ናቸው።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ለማፍለቅ በትኩረት በተሰራው ስራ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል።
በሄክታር ሰባት ኩንታል ብቻ የነበረውን የቡና ምርታማነት በምርምር በፈለቀ ዝርያ 28 ኩንታል አድርሰናል ብለዋል።
ውጤቱ ሊመጣ የቻለው የቡና ዝርያዎችን በመለየት የተሻለ ምርት ሊሰጡ የሚችሉ ዝርያዎችን በማዳቀል እንደሆነም ተናግረዋል።
የዲቃላ ቡና ዝርያን ቆርጦ በመውሰድ (ቲሹካልቸር ቴክኖሎጂ) ብዙ ችግኞችን ለማዘጋጀት የሚያስችል ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የዲቃላ ዝርያን ከአንድ ጊዜ በላይ መጠቀም የማይቻል በመሆኑ ሁልጊዜ የዝርያ ማዘጋጀት ስራ እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፤ ለዝርያ ማሻሻል በተሰጠው ትኩረት ችግኙን በብዛት በማዘጋጀት ለአርሶ አደሩን የማድረስ ስራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።