Fana: At a Speed of Life!

የብድርና ቁጠባ ተደራሽነትን በማስፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ…

በሀገር አቀፍ ደረጃ በመቋቋም ላይ የሚገኘው ፎርቹን ኃላፊነቱ የተወሰነ የብድርና ቁጠባ ሕብረት ሥራ ማህበር ጠቅላላ ጉባዔውን በአዲስ አበባ አካሂዷል፡፡

በዚህ ወቅትም የብድር እና ቁጠባ ተደራሽነትን በማስፋት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡

የፌዴራል ህብረት ሥራ ኮሚሽን በመድረኩ ባስተላለፈው መልዕክት ÷ የብድርና ቁጠባ ህብረ ሥራ ማህበራት ኢኮኖሚያዊ አቅምን በማሳደግ ሀገራዊ ብልፅግና እንዲረጋገጥ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብሏል፡፡

የአከባቢን ፀጋ መሠረት በማድረግ ህብረት ሥራ ማህበራትን የማደራጀት ተግባር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አመልክቷል፡፡

ማህበራት ደህንነታቸው ተጠብቆ፣ የአባላቱ ተጠቃሚነት ተረጋግጦና ሕግን አክብረው እንዲሰሩ ለማድረግ ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁሟል፡፡

የፎርቹን ብድርና ቁጠባ ኮር አባልና አስተባባሪ አቶ ወንድወሰን አያሌው ÷ ማህበሩ ከአባላት ምልመላ ጀምሮ አካታች፣ የመመዘኛ መስፈርቶችን ያሟላና አዋጭነቱ የተጠና መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ ማህበሩ የተለያየ የትምህርት ደረጃና ልምድ ያላቸው ከ900 በላይ አባላት እንዳሉት ነው የተናገሩት፡፡

የፎርቹን ብድርና ቁጠባ ዋና አላማ በጥቃቅን እና አነስተኛ የተደራጁ ኢንተርፕራይዞችን በማገዝ ውጤታማ ማድረግ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

አባላቱ ቆጥበው ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ ይመቻቻል ያሉት አቶ ወንድወሰን ÷ በአፍሪካ ግንባር ቀደም የብድር እና ቁጠባ ማህበር ለመሆን እንሰራለን ብለዋል፡፡

ማህበሩ አሁን ላይ 200 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል እንዳለው እና በቀጣይ ወደ ሥራ በመግባት የአባላቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በጉባዔው የማህበሩ የሥራ አስፈጻሚ አባላት እና ሌሎች ኮሚቴዎች ምርጫ ተካሂዶ መጠናቀቁ ተመላክቷል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.