Fana: At a Speed of Life!

ምሁርነት ያለፈውንና የአሁኑን በቅጡ የሚረዳ፤ መጪውን የሚያመላክት ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምሁርነት ያለፈውንና የአሁኑን በቅጡ የሚረዳ እንዲሁም መጪውን የሚያሰላስልና የሚያመላክት ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ “የምሁራን ሚና ለሀገራዊ ብልጽግና” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ጽሑፋቸው÷ የምሁራን ሚና ለሀገር ብልጽግና ከፍተኛ ሚና የሚኖረው በዘርፉ የሚሰጠውን አመራር አውቆና ተረድቶ መገልገል ሲቻል ነው ብለዋል፡፡

ምሁራን የጋራ ትርክት በመፍጠር የበለጸገችና ከድህነት የተላቀቀች ኢትዮጵያን ለማየት የሚጠበቅባቸውን ምሁራዊ አመራር መስጠት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

መሪ ማለት በመጀመሪያ ራሱን ያሸነፈ፣ በውስጥ ያለውን ድምጽ ማዳመጥና መለየት የሚችል እንዲሁም ከራሱ ጋር መወያየትና በዚህም ራሱን ማሸነፍ የሚያስቀድም ነው ብለዋል፡፡

ከራሱ ጋር ከተነጋገረ እና ራሱን ካሸነፈ በኋላም ጊዜን በመዋጀትና ነባራዊ ሁኔታውን በማገናዘብ እያንዳንዱን ጊዜ ለተገባ ዓላማ ማዋል ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም መሪ ስለሃሳብ ያለው አፍቅሮት፣ መከፈት እና በሃሳብ ለማመን ያለው ዝግጁነት ወሳኝ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ምሁር ሃሳብ የሚገበይና የሚሸጥ ብቻ ሳይሆን የታለመውን እቅድ ለማሳካት ግብ የሚያስቀምጥ መሆን እንዳለበት አብራርተዋል፡፡

ይህን ማድረግ ከቻለም ከራሱ አልፎ ሌሎችን መጥቀም የሚችልና ተጽእኖ የማሳደር ብቃት ያለው እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡

ምሁራን አዎንታዊ ተጽእኖ በመፍጠር የለውጥ ትልም ነድፈው አመራር መስጠት አለባቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በዚህም ሰዎችን በማብቃት ውጤት ማምጣት ሲቻል የመሪነት ብቃት ተጎናጽፈዋል ይባላል ብለዋል፡፡

መሪነት በጊዜና በዘመን ላይ መሰልጠን እንዲሁም ከጊዜ ጋር ያለን እሽቅድድም ሳይቀደሙ መኖር ማለት ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ከሶሶቱ የምሁርነት አንጓዎች መካከል የመጀመሪያው መሪዎች የሃሳብ መሪዎች ወይም ምሁራን ናቸው፣  እነዚህም ያለፈውን ወይም ያለንበትን ጊዜ የሚረዱ እና መጪውን ማየት የሚችሉ፣ ዛሬን አበክረው የሚሰሩ ናቸው ብለዋል፡፡

ምሁራን ወደ ፊት ለመስፈንጠር ወደኋላ ያለውን ሄደው በቅጡ መገንዘብ እና መረዳት እንደሚጠበቅባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጽሑፋቸው አብራርተዋል፡፡

ትናንትናን መዳሰስና ነገን ማየት ብቻውን በቂ አይደለም ፤ የሃሳብ ምሁር ለመሰኘት ዛሬን ጠንቅቆ መረዳትና መስራት ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡

ሃሳብ የለውጥ ሃይል ሲሆን ምሁራን ደግሞ የለውጥ ወኪል ናቸው፤ ምሁራን ሃሳብን ወክለው በፖለቲካና ኢኮኖሚ አውድ እንዲሁም በሰዎች መስተጋብር ውስጥ የሃሳብ ወኪል ሆነው ሊንቀሳቀሱ ይገባል ብለዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.