ምሁራን በሃሳብ የበላይነት የሚያምኑና አዳዲስ ፈጠራዎችን የሚያበረክቱ ሊሆኑ ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምሁራን የሃሳብ ልዩነታቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ በመፍታት ለሃሳብ የበላይነት የሚገዙና አዳዲሰ ነገሮችን የሚፈጥሩ ሊሆኑ ይገባል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ “የምሁራን ሚና ለሀገራዊ ብልጽግና” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ከታዳሚ ምሁራን ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ÷ በኢትዮጵያ መጀመሪያ ላይ የነበሩት ምሁራን እሳቤ ከሞላ ጎደል ኢኮኖሚን ያስቀደመ እንደነበር አንስተዋል፡፡
የኢኮኖሚው ማዕከልም መሬት እንደነበርና መሬት ያለው ሰው ደግሞ ሃብታም እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡
በዚህ ወቅትም የምሁራን እሳቤ ሥርዓትን ማፍረስ ሳይሆን ፍትሃዊ የሆነ የሃብት ክፍፍል እንዴት ሊኖር ይቻላል የሚለው እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
የወቅቱ ምሁራን ስለ ሀገር ክብር ታላቅ መረዳት የነበራቸውና ወላጆቻቸውን የሚያከብሩ፤ ለማሳመንም የሚጥሩ ነበሩ ነው ያሉት፡፡
በቀጣይ የመጡ ተፋላሚ ትውልዶች ደግሞ የቀደሙትን የምሁራን ባህሪያት የማያሟሉና ራሳቸውን የማያዳምጡ፤ ፖለቲካን ያስቀደሙ እንደነበሩ አስረድተዋል፡፡
አሁን ላይ ከሁለቱም የቀደመ ምሁራን ጠቃሚውን በመውሰድ ማዕከል ያደረገ እና ፍጥነትን ያስቀደመ አካሄድ ማራመድ አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምሁራን አንዱ ችግራቸው ከውጭ ሀገራት ሄደው ያዩትን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር አስተሳስሮ ከመተግበርና ከማስፋፋት ይልቅ ሙሉውን ለመኮረጅ መሞከራቸው ነው ብለዋል፡፡
ማሕበረሰቡን በሥራ ማሳመን የሚቻለው በሒደት ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን ጠቁመው÷ በዚህ አግባብ የአሁን ጊዜ ምሁራን ነገሮችን በስክነት ማመዛዘንና መወሰን ከዚያም ተግብረው ለውጤቱ ሃላፊነት ሊወስዱ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
ምሁራን እነሱ የሚያስቡትና የሚያቅዱት ሌላም ቦታ እንዳላ በመረዳት ሃሳብን ለማፋጨትና ለማንጠር ቁርጠኛ ሊሆኑ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ምሁራን በምርምር አዳዲስ ነገሮችን ለማሕበረሰቡ ለማበርከት ያለማቋረጥ መትጋት አለባቸው፤ ለመማርና ለመጠየቅ ክፍት መሆን አስፈላጊ ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ምሁራን የጋራ መድረክ በመፍጠር ያላቸውን የሃሳብ ልዩነት በመነጋገር የጋራና ገዢ የሆነ ሃሳብን መያዝ መልመድ እንዲሁም በሃሳብ የበላይነት ማመንን ማዳበር እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡
የጋራ ሃሳብን በመውሰድ ለአንድ አላማ በትብብር መስራትና መደመር ለሁሉም ዘርፍ ስኬታማነት ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በቂምና በቀል መስራት ውጤታማ አያደርግም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ በተማረበት ዘርፍ ምንም አበርክቶ ሳይኖረው ምሁር ነኝ ማለት ትክክል አይደለም ብለዋል፡፡
አሁን ያለው ትውልድ በጣም ተስፋ ያለውና የሚበረታታ እንደሆነ ገልጸው፥ አንዳንድ ልጆች የሚያስቡበት ደርዝና ልክ አስገራሚ መሆኑን አውስተዋል፡፡
የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በሚኖረው አሉታዊ ተጽዕኖ አልሰጋም፤ የሚያሰጋው እንቅልፋችን ነው፤ ልጆቻችንን በሚገባ ካዘጋጀን በትክክለኛው መንገድ ለመጠቀም አንቸገርም ሲሉ አብራርተዋል፡፡
የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሥራ ይቀማል የሚል ስጋት የለኝም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የሰው ልጆች መስራት የማይገባቸውን ሥራዎች ግን ይሰራል ነው ያሉት፡፡
ይሁን እንጂ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በትክክል ለመተግበርና ለመጠቀም ቀድመን ትውልዱ ላይ መሰረት መጣል አለብን ብለዋል፡፡
አሁን ያለው ትውልድ ከፊቶቹ ኢኮኖሚና ፖለቲካን ከሚያስቀድሙት በተሻሻለ መልኩ በሃሳብ የሚያምን መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የሃሳብ የበላይነትን የሚያምን ትውልድ ይሻገራል፤ ይሄንን የማይቀበል ደግሞ ኋላቀር ሊባል ይችላል ነው ያሉት፡፡
በየጊዜው የሚዘምነው ቴክኖሎጂ ሥራን የሚያቀል በመሆኑ ከመስጋት ይልቅ በአግባቡ መጠቀም ላይ ማተኮርና መስራት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ