የአየር ኃይል ምስረታ በዓል የኢትዮጵያን ገፅታ በሚያጎላ መልኩ ይከበራል – ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የአየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የኢትዮጵያን ገፅታ በሚያጎላ መልኩ ይከበራል አሉ።
ዋና አዛዡ ከተቋሙ ከፍተኛ መኮንኖች ጋር ባደረጉት ውይይት እንዳሉት÷ በዓሉ ከመጪው ጥር 15 እስከ 19 ቀን 2018 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል የዘመናዊነትና የሉዓላዊነት አርማ ሆኖ የዘለቀበትን 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የሀገሪቱን ክብርና የተቋሙን ግዙፍ አቅም በሚመጥን መልኩ ለማክበር ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዓሉ አየር ኃይላችን የቴክኖሎጂ ቁንጮና የጥንካሬያችን መገለጫ መሆኑን በተግባር የምናሳይበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ብለዋል።
አከባበሩ ዝም ብሎ መታሰቢያ ብቻ ሳይሆን የተቋሙን የላቀ ቁመና ለዓለም የሚያሳይ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚፈጥር እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝብ በአየር ኃይል ላይ ያለው መተማመን እንዲጎለብት የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመንካት ለሚያስቡ ኃይሎች የተቋሙን ዝግጁነትና ቁመና ለማሳየት ያለመ እንደሆነም አመላክተዋል።
የአየር ኃይሉ ከፍተኛ አመራሮች በበኩላቸው÷ ተቋሙ በሪፎርም ታድሶና በዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች ተገንብቶ በሚገኝበት ወቅት 90ኛ ዓመቱን ማክበሩ ልዩ ትርጉም እንዳለው መናገራቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።
በዓሉን በላቀ የዲሲፕሊንና የዝግጁነት ደረጃ ለማክበር ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።