የጥምቀት በዓል አከባበር በተለያዩ ሀገራት…
አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጥምቀት ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ መጠመቁን በማሰብ የሚከበር በዓል ነው።
በዓሉን በዓለም ዙሪያ ያሉ አብዛኘው የክርስትና እምነት ተከታዮች በየሀገራቸው በተለያዩ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ሥርዓት ያከብሩታል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን፣ ሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና የሰርቢያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የጥምቀት በዓልን በዛሬው ዕለት ነው ያከበሩት፡፡
ጥምቀትን በድምቀት ከሚያከብሩ ሀገራት መካከል የሆነችው ሩሲያ በበዓሉ ምዕመኑ በበረዷማ ውሃ ውስጥ ሦስት ጊዜ ሙሉ በሙሉ በመስመጥና በመውጣት ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቁን በማሰብ አክብረዋል፡፡
በኢትዮጵያም የጥምቀት በዓል በሃይማኖታዊ እና በባህላዊ ሁነቶች በድምቀት ተከብሮ ውሏል።
በኢትዮጵያ በየዓመቱ በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት መካከል የሆነው የጥምቀት በዓል አከባበር ሥነ ሥርዓት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ ይታወቃል።
በሌላ በኩል የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን ጨምሮ ሉተራን፣ አንጀሊካ እና ሌሎች ምዕራባውያን አብያተ ክርስቲያናት ከኢትዮጵያ ቀድመው በኢትዮጵያውያኑ ታሕሣሥ 28 ቀን አክብረዋል።
ጥምቀት ስፔንን ጨምሮ በርካታ የላቲን አሜሪካ ሀገራት በተለያዩ የአደባባይ ትዕይንቶች እርስ በእርስ ስጦታ በመለዋወጥ በጋራ የሚያከብሩበት በዓል ነው፡፡
እንዲሁም ቼክ ሪፐብሊክ፣ ግሪክ እና ቡልጋሪያም በረዷማ በሆነ ወንዝ በመዋኘት ጥምቀትን ሲያከብሩ÷ ጣሊያን ደግሞ በጥምቀት ዋዜማ ለልጆች ጣፋጭ ምግቦችና ስጦታ የመስጠት ባሕል አላቸው፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያንና ኤርትራን ጨምሮ ሩሲያ፣ ዩክሬን፣ ስፔን፣ ሜክሲኮ፣ የምስራቅ አውሮፓ ሀገራት እንዲሁም በአውሮፓና አሜሪካ የሚገኙ ክርስትና እምነት ተከታዮች የጥምቀት በዓሉን በልዩ ልዩ ክዋኔዋች በድምቀት አክብረዋል።
በሶስና አለማየሁ