የውስጥና የውጭ የስጋት ኃይሎችን እንቅስቃሴ የሚቀለብሱ ስምሪቶች ተከናውነዋል – የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የውስጥና የውጭ የስጋት ኃይሎችን እንቅስቃሴ የሚቀለብሱ ስምሪቶች ተከናውነዋል አለ፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የ2018 የመጀመሪያ ግማሽ በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጻም ግምገማ መድረክ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ሀገራዊ የጸጥታ ሁኔታን የማጽናት፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምረቃን ጨምሮ የአደባባይ ክብረ በዓላት እንዲሁም ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች በስኬት እንዲጠናቀቁ የማድረግ፣ የተቋማዊ የሪፎም አጀንዳዎችን የመከለስና ለጠቅላላ ምርጫው ስኬት የሚረዱ ዝግጅቶች በላቀ ደረጃ መፈጸማቸው ተመላክቷል፡፡
ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በመሆን በተከናወኑ ስምሪቶች በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የስጋት ኃይሎችን በማዳከም ረገድ መሰረታዊ ለውጥ መመዝገቡ ነው የተገለጸው፡፡
የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ኃይሎችም ትጥቅ እየፈቱ ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ የሚረዱ ስምሪቶች መከናወናቸው ተጠቅሷል፡፡
በውጭ ሀገር የመረጃ ስምሪት በተከናወኑ ስር ነቀል የለውጥ ሥራዎች በሀገራዊ ጥቅምና ደኅንነት ላይ የሚቃጡ ስጋቶችን መቀልበስና መልካም አጋጣሚዎችን መጠቀም መቻሉ ተመልክቷል።
በዓለም ዓቀፋዊና ቀጣናዊ ተለዋዋጭ የደኅንነት ምህዳር ውስጥ የኢትዮጵያን ከፍታና የሕዝቦቿን ተጠቃሚነት የሚያረጋገግጡ ስትራቴጂክ ድሎች እየተመዘገቡ መሆኑ ተነስቷል፡፡
ተቋሙ የተሰጡትን የመረጃ፣ የደኅንነትና የሥነ ልቦና ጦርነት የተልዕኮ ሥራዎች በላቀ መንገድ የመፈጸም አቅሙ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉ ተገልጿል፡፡
በዚህም ስጋቶችን ከመቀልበስ ባሻገር ቀድሞ ችግሮችን በመለየትና አዝማሚያዎችን በመተንተን ድንገተኛ የሚባሉ የደኅንነትና የፀጥታ ክፍተቶችን ማስቀረት ስለመቻሉ በመድረኩ ተጠቅሷል፡፡
አሁንም ሰላምና ፀጥታ የማጽናት ሂደቱ ያልተዋጠላቸው የውስጥና የውጭ ኃይሎች የፈጠሩት ግንባር እንዲሁም ቀጣናውን የኃይል አሰላለፍ ፍጥጫ በማድረግ ረገድ የሚታዩት እንቅስቃሴዎች ተግዳሮቶች መሆናቸው በመድረኩ ተብራርቷል፡፡
ይህን የሚቀለብስ ተቋማዊ ዝግጁነት መገንባቱንም የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል፡፡
ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት በምርጫ ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የስጋት ምንጮችን ለመለየት የዳሰሳ ጥናት ማካሄዱንና በዳሰሳ ጥናቱ የተለዩ ስጋቶችን ለመቀልበስ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂ፣ በስልጠናና በሥነ ልቦና ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
በሚቀጥሉት ወራት የሚከናወኑት የአፍሪካ ህብረት ጉባዔና ሌሎች ትላልቅ ሁነቶች እንዲሁም ጠቅላላ ምርጫው በስኬት እንዲከናወን በተሟላ የሰው ኃይል፣ የቴክኖሎጂና የሎጂስቲክስ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡