Fana: At a Speed of Life!

አርሰናል ከማንቼስተር ዩናይትድ – ተጠባቂው ፍልሚያ

አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የ23ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ዛሬ በሚደረጉ አምስት ጨዋታዎች ይጀምራል፡፡

ምሽት 12 ሰዓት ላይ ማንቼስተር ሲቲ በሜዳው ኢትሃድ በውድድር ዓመቱ እስካሁን አንድ ጨዋታ ብቻ ካሸነፈው ወልቭስ ጋር ይጫወታል፡፡

በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት አራት ጨዋታዎች በአንዱም ማሸነፍ ያልቻለው ማንቼስተር ሲቲ ወደ ድል ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ማንቼስተር ሲቲ ሁሉንም በማሸነፍ የበላይነት አለው፡፡

ማንቼስተር ሲቲ ጨዋታውን የሚያሸንፍ ከሆነ ነጥቡን ወደ 46 ከፍ በማድረግ አርሰናል እስኪጫወት ድረስ ከአርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አራት ማጥበብ ይችላል፡፡

በተመሳሳይ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ፉልሃም ከብራይተን እንዲሁም በርንሌይ ከቶተንሃም ሆትስፐር ይገናኛሉ፡፡

ምሽት 2 ሰዓት 30 ላይ ሊቨርፑል ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ከቦርንማውዝ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል፡፡

ያለፉትን ተከታታይ አራት የሊጉን ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ያጠናቀቀው ሊቨርፑል ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይፋለማል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ሊቨርፑል ሁሉንም በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል፡፡

ከእነዚህ ጨዋታዎች አስቀድሞ ቀን 9 ሰዓት 30 ላይ ዌስትሃም ዩናይትድ ከሰንደርላንድ የሚገናኙ ይሆናል፡፡

የሊጉ ጨዋታዎች ነገ ቀጥለው ሲደረጉ የሊጉን መሪ አርሰናል ከማንቼስተር ዩናይትድ የሚያገናኘው ጨዋታ ከወዲሁ ተጠባቂ ሆኗል፡፡

በሊጉ ያለፉትን ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻለው በአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ የሚመራው አርሰናል ወደ አሸናፊነት ለመመለስና መሪነቱን ለማጠናከር ይፋለማል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት በማይክል ካሪክ እየተመራ በከተማ ተቀናቃኙ ማንቼስተር ሲቲ ላይ ድል የተቀዳጀው ተጋጣሚው ማንቼስተር ዩናይትድ በበኩሉ በነገው ጨዋታ ላይ ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች አርሰናል ሦስቱን በማሸነፍ የበላይነት የያዘ ሲሆን፥ በአንዱ አቻ ተለያይተው በቀሪው አንድ ጨዋታ ማንቼስተር ዩናይትድ ድል ቀንቶታል፡፡

አርሰናልን ከማንቼስተር ዩናይትድ የሚያገናኘው የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ እሁድ ምሽት 1 ሰዓት 30 ላይ በኢምሬትስ ስታዲየም ይጀምራል፡፡

ኒውካስል ዩናይትድ ከአስቶንቪላ፣ ክሪስታል ፓላስ ከቼልሲ እንዲሁም ብሬንትፎርድ ከኖቲንግሃም ፎረስት ነገ 11 ሰዓት የሚደረጉ የሊጉ ጨዋታዎች ናቸው፡፡

የ23ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር ሰኞ ምሽት 5 ሰዓት ላይ ኤቨርተን ከሊድስ ዩናይትድ በሚያደርጉት ጨዋታ ይጠናቀቃል፡፡

ሊጉን አርሰናል በ50 ነጥብ ሲመራው ማንቼስተር ሲቲ እና አስቶንቪላ በተመሳሳይ 43 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡

ሊቨርፑል በ36፣ ማንቼስተር ዩናይትድ በ35 እንዲሁም ቼልሲ በ34 ነጥቦች በመሰብሰብ ከ4ኛ እስከ 6ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡

በወንድማገኝ ፀጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.