ከ27 ሺህ በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች …
አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደሀንነት አስተዳደር (ኢመደአ) በስድስት ወራት ከተሞከሩ 27 ሺህ 773 የሳይበር ጥቃቶች 99 ነጥብ 03 በመቶ የሚሆነውን ማክሸፍ ተችሏል አለ።
ተቋሙ የ2018 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ አካሂዷል።
የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ÷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀያየሩ የመጡትን የሳይበር ጥቃት ባህሪያት ግምት ውስጥ በማስገባት የመከላከል አቅማችን እየዘመነ ይገኛል ብለዋል፡፡
የሳይበር ደህንነት ሥጋቶችን ቀድሞ ለመለየትና ምላሽ ለመስጠት የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶችን ለማበልጸግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራተጂ መሠረት የሚሆኑ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰው÷ የመንግሥት ተቋማትን ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ አሠራራቸውን ዲጂታላይዝ የሚያደርጉ የቴክኖሎጂዎችን እንዲታጠቁ መደረጉን ገልጸዋል።
ለአብነትም ገቢዎች ሚኒስቴር የኢ-ኢንቮይስ፣ አዲስ አበባ ገቢዎች የሰውነት ላይ ካሜራ፣ እንዲሁም ፌደራል ፖሊስ የተቀናጀ የሰው ሀብትና የሰነድ አስተዳደር ሲስተሞችን በማልማት አገልግሎታቸውን እንዲያዘምኑ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶችን ለማክሸፍ እየተሰራ መሆኑን አንስተው፤ በስድስት ወራት ከተሰነዘሩ 27 ሺህ 773 የሳይበር ጥቃቶች ውስጥ 99 ነጥብ 03 በመቶ የሚሆነውን ማለትም 27 ሺህ 505ቱን ማክሸፍ መቻሉን ገልጸዋል።
የዲጂታል ፎረንሲክ ምርመራን በተመለከተ አስተዳደሩ ከቀረቡለት 253 የምርመራ ጥያቄዎች ውስጥ ለ245ቱ ምላሽ መስጠቱ ተመላክቷል፡፡