Fana: At a Speed of Life!

የኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የልማት ርዕይ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አለው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የልማት ርዕይ ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አለው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ።

የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽንን የጎበኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት÷ ይህ ተቋም ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የልማት ርዕይ ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አለው።

ኢትዮጵያ እጅግ ከፍተኛ በሆነ እምቅ አቅሟ እና በተትረፈረፈ ተፈጥሯዊ ሀብቷ ለረጅም ጊዜ እንደምትታወቅ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ ምዕራፍ ደግሞ እነዚህን ሀብቶች ወደ ተጨባጭ ልማት፣ የቴክኖሎጂ እድገት እና ወደ ጋራ ብልጽግና መለወጥ ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቁመዋል።

አስተማማኝና ዘላቂ የኃይል አቅርቦት ለኢንዱስትሪ፣ ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለዲጂታል መሠረተ ልማትና ለአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ወሳኝ መሆኑንም አስረድተዋል።

የኒውክሊየር ቴክኖሎጂ ደግሞ የኃይል ዋስትናን በማጠናከር እየገሰገሰ ያለውን ፍላጎት ለማሟላት ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸው፤ ከኃይል ምርት ባለፈ በጤና፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፎች ለሀገራዊ ልማትና ለቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ መሠረታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ለብሔራዊ የኒውክሊየር ኃይል ፕሮግራም አስፈላጊ የሆኑትን ተቋማዊ እና ቴክኒካዊ መሠረቶች በመጣል ይህንን ርዕይ ለማሳካት ስትራቴጂካዊ ሚና አለው ነው ያሉት።

በዚህም ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት፣ ሳይንሳዊ ምርምርን ማስፋፋትና ተቋሙን ዕውቀትን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ቁልፍ ተግባራት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ይህም ብሔራዊ አቅምንና ልዩ ሙያዊ ብቃትን በማዳበር የኒውክሊየር ኃይል ልማት ሰላማዊ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ አስተማማኝ እና ዘላቂ በሆነ መንገድ በኃላፊነት ስሜት እንዲከወን እንደሚያግዝ አስገንዝበዋል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.