በመጪው ምርጫ የሴቶችና የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያንን ተሳትፎ ትርጉም ባለው ደረጃ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፡፡
በሴቶችና ወጣቶች የምርጫ ተሳትፎና በማህበራዊ አካታችነት ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ባለፉት ዓመታት የዜጎችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ1987 ዓ.ም 2 ነጥብ 7 በመቶ የነበረው የሴቶች ውክልና በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ወደ 41 ነጥብ 2 በመቶ ማደጉ ለዚህ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያንና ለችግር ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተቀናጀ ተሳትፎ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጎልበት፣ ለፍትሃዊ ውክልናና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ ንዋይ በበኩላቸው፥ ቦርዱ አካታችነትን ለማረጋገጥ ካለፉት የምርጫ ጊዜያት በተሻለ መልኩ ዝግጅቶችን ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
ከምዝገባ ወቅት ጀምሮ ልዩ መለያዎችን በማዘጋጀት አረጋዊያን፣ አካል ጉዳተኞችና ሴቶች ቅድሚያ እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ ሲሆን፥ ለሴት እጩዎች የሚያስፈልገውን የድጋፍ ፊርማ ቁጥር ዝቅ እንዲል ከማድረግ ጀምሮ በርካታ እድሎች ተመቻችተዋል ነው ያሉት፡፡
ይህ ጥረት ፍሬ እንዲያፈራ ሲቪል ማህበራት፣ መገናኛ ብዙሃንና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በማህሌት ካሳሁን