ቱኒዚያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድ ትስስር ማጠናከር እንደምትፈልግ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከቱኒዚያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሀመድ አሊ ናፋቲ ጋር ተወያይተዋል።
ሚኒስትሮቹ በውይይታቸው በሀገራቱ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ላይ በትኩረት መክረዋል፡፡
ሞሀመድ አሊ ናፋቲ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በንግድና በኢንቨስትመንት ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም ሁለቱ ወገኖች በሌሎች የሁለትዮሽ እና አሕጉራዊ የጋራ ፍላጎቶች ዙሪያ ሃሳብ ተለዋውጠዋል።
በተመሳሳይ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከቡሩንዲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤድዋርድ ቢዚማን ጋር የሁለትዮሹን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
በውይይቱ ላይ በሁለቱ ሀገራት መካከል የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ በቅርቡ በማካሄድ የተፈረሙ የትብብር ስምምነቶችን አፈጻጸም ለመገምገም እና አዳዲስ የትብብር መስኮችን ለመለየት ተስማምተዋል።
ውይይቱ ከ48ኛው የአፍሪካ ሕብረት መደበኛው የሥራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ ጎን ለጎን ነው የተካሄደው።