እስከ 60 ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያለው የተንዳሆ መስኖ መሠረተ ልማት …
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) የተንዳሆ መስኖ መሠረተ ልማት እስከ 60 ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም አለው አሉ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የተንዳሆ መስኖ ልማት ማጠናቀቂያ እና መልሶ ግንባታ ፕሮጀክትን መርቀዋል።
አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ ባለፉት ጥቂት ወራት በመንግሥት ያላሰለሰ ድጋፍና በክልሎች ቁርጠኝነት እንዲሁም በጠንካራ የፕሮጀክት አመራር አምስት የመስኖ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።
የተንዳሆ መስኖ ልማት ማጠናቀቂያ እና መልሶ ግንባታ ፕሮጀክት ስኬት የግብርና ምርታማነት የተስፋ ምንጭና የኢኮኖሚ መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ በመጠናቀቁ የአካባቢው ማህበረሰብ ከዝናብ ጥገኝነት ተላቅቆ በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ በማምረት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለተጀመረው ጥረት ላቅ ያለ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ከ15 ዓመታት በፊት ቢጀመርም የማህበረሰቡ የስጋት ምንጭ ከመሆን ያለፈ ጥቅም ሳይሰጥ መቆየቱን አስታውሰው፤ የውሃ ፍሰቱን መቆጣጠር የሚያስችል ሥርዓት በአግባቡ ስላልተዘረጋለት ተጨማሪ ችግር እንደነበረበት ጠቅሰዋል።
አሁን ላይ የፕሮጀክቱ ውስብስብ ችግሮች ተቃለው ወደ ሥራ መግባቱን ማንሳታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የግድቡን ሁኔታ በማጥናት የውሃ ማስተንፈሻ ችግሮች እንዲስተካከሉ መደረጉንና 40 ኪሎ ሜትር የካናል ዕድሳት ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።
ማህበረሰቡንና ካናሎቹን ከጎርፍ ለመከላከልም 27 ኪሎ ሜትር የድጋፍ ግንብ ተገንብቷል ብለዋል።
60 ሺህ ሄክታር የማልማት አቅም ያለው መሰረተ ልማቱ በአሁኑ ወቅት 33 ሺህ ሄክታር ለማልማት ዝግጁ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ 23 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን አስረድተዋል።