የተንዳሆ መስኖ መሠረተ ልማት የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ የሚያሰቀር ነው – አቶ አወል አርባ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተንዳሆ መስኖ መሠረተ ልማት በአፋር ክልል የተለያዩ ወረዳዎች የሚከሰተውን ድርቅ እና የጎርፍ አደጋ የሚያስቀር ነው አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የተንዳሆ መስኖ ልማት ማጠናቀቂያ እና መልሶ ግንባታ ፕሮጀክትን መርቀዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የተንዳሆ መስኖ መሠረተ ልማት የዱብቲ እና የሠመራ ሎጊያ ከተሞችን ጨምሮ ስድስት ወረዳዎችን በቀጥታ ጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።
የአፋር ሕዝብ በክረምት ወቅት ጎርፍ እንዲሁም በድርቅ ወቅት በውሃ እጥረት ጉዳት ሲደርስበት መቆየቱን አስታውሰው÷ የተንዳሆ የተንዳሆ መስኖ መሠረተ ልማት እነዚህን ተፈጥሯዊ ክስተቶች የሚያስቀርና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
ተንዳሆ ግድብ ውሃ ሲሞላ የማስተንፈሻ ቦዩ የመቆጣጠሪያ ሥርዓት ችግር የነበረበት በመሆኑ ማህበረሰቡ ላይ ትልቅ የጎርፍ አደጋ ስጋትትን ደቅኖ እንደነበር አስታውሰዋል።
ነገር ግን ፕሮጀክቱ አሁን ላይ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት መብቃቱ ስጋቱን እንደሚያስቀር ገልጸዋል።
የፌዴራል መንግሥት የተንዳሆ መስኖ ልማት ከችግርና ስጋት እንዲወጣ የማጠናቀቂያ እና መልሶ ግንባታ በማከናወኑ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ወደሚያደርግ የልማት አውታር መልሶታል ብለዋል፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የግድቡን ሁኔታ በማጥናት የውሃ ማስተንፈሻ ችግሮች እንዲስተካከሉ ተደርጓል፤ 40 ኪሎ ሜትር የካናል ዕድሳት ሥራ ተሰርቷል።
ማህበረሰቡንና ካናሎቹን ከጎርፍ ለመከላከልም 27 ኪሎ ሜትር የድጋፍ ግንብ ተገንብቷል።
60 ሺህ ሄክታር የማልማት አቅም ያለው መሰረተ ልማቱ በአሁኑ ወቅት 33 ሺህ ሄክታር ለማልማት ዝግጁ ሆኗል።
በለይኩን ዓለም