የእናቶች ጤና አገልግሎትን በዲጂታል አማራጭ ክትትል ማድረግ…
አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የእናቶች ጤና አገልግሎትን በዲጂታል አማራጭ ክትትል ማድረግ በእርግዝና፣ ወሊድና ድህረ ወሊድ ጊዜ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመለየትና ምላሽ ለመስጠት ያግዛል አለ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ።
የክልሉ ጤና ቢሮ የጤናማ እናትነት ወር ማጠቃለያ መርሐ ግብር “ፈጠራና ዘላቂ ፋይናንስ ለጤናማ እናትነት” በሚል መሪ ሐሳብ አካሂዷል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ መና መኩሪያ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ጤናማ የእርግዝና፣ ወሊድና ድህረ ወሊድ አገልግሎቶችን ለሁሉም እናቶች ተደራሽ በማድረግ የእናቶችና ጨቅላ ህጻናት ሞት መቀነስ ይገባል።
ለሁሉም እናቶች የተሟላ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ቢሮው የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸው÷ የእናቶችና ጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለዚህም ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ የጤና አቅም ግንባታ እንዲሁም ተቋማትን በግብዓት ማሟላትና ደም ማሰባሰብ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
የእናትነት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ38ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ20ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።
በጌትነት ጃርሳ