በሕብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ኢትዮጵያ የውሃ ሃብቷን በፍትሃዊነት ለመጠቀም ያላትን ዝግጁነት ገልጻለች – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ኢትዮጵያ የውሃ ሃብቷን በፍትዊነት ለመጠቀም ያላትን ዝግጁነት አስረድታለች አለ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ ተስፋሁን ጎበዛይ የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔን እና የጣሊያን አፍሪካ ጉባዔን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ የተካሄደውና የከተማዋን የዲፕሎማሲ ማዕከል ቀጣይነት የሚያሳየው የጣሊያን አፍሪካ ጉባዔ በስኬት መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
የጣሊያን አፍሪካ ጉባዔ ዋና አላማ በጣሊያን እና አፍሪካ መካከል ያለውን ግንኙነት ስትራቴጂያዊ በሆነ መልኩ ወደ አጋርነት ለማሳደግ ለሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በጉባዔው አጋርነት ማለት ሁለት አስተዋጽኦ ያላቸው አካላት በጋራ የሚቆሙበት ዓውድ እንደሆነ መናገራቸው ጠቅሰዋል፡፡
በዛሬው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትሯ በሕብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግርም አፍሪካ በመጻኢው ዓለም ላይ የተለየ ቦታ እንዳላት አብራርተዋል ነው ያሉት፡፡
ለአብነትም የአፍሪካ አሕጉር ያልተነካ እምቅ የተፈጥሮ ሃብት፣ ወጣት እና የተማረ የሰው ሃይል ያለው መሆኑን እንዳነሱ አስረድተዋል፡፡
በጉባዔው በስድስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት መደረጉን ጠቁመው ÷በዚህም በጤና፣ ትምህርት፣ ኢነርጂ፣ ግብርና እና ውሃ ዘርፎች ላይ ምክክር መደረጉን አመልክተዋል፡፡
ከኢነርጂ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ምንጮች የታዳሽ ኃይል ተጠቃሚነትን ለማጠናከር በትኩረት እየሰራች እንደምትገኝ አብራርተዋል፡፡
በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከውሃ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሃብት መርህን በተከተለ መልኩ ለመጠቀም ያላትን ዝግጁነት አብራርተዋል ብለዋል፡፡
በዚህም ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እስከ ፍትሃዊ እና በሕግ አግባብ የሚመለስ የባሕር በር ባለቤትነት ድረስ ያለውን ሒደት በዝርዝር አስረድተዋል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም በግብርና በተለይም በስንዴ ራስን ለመቻል የተደረገውን ጥረት እና በዚህም ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን እንዳስረዱ ነው የገለጹት፡፡
እንዲሁም በዲጂታላይዜሽን ዘርፍ በፋይዳ እና በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ውጤታማ ሥራ መከናወኑን አጽንኦት መስጠታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገራትን ሁለንተናዊ ትስስርን ይበልጥ ለማጠናከር በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሕዝቦችን ከማገናኘት ባለፈ የገበያ ትሰስርን በመፍጠር የኢኮኖሚ እድገትን እያጠናከረ እንደሚገኝ ማውሳታቸውን ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ሥራውን ይበልጥ ለማሳደግ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግዙፍ የሆነውን አውሮፕላን ማረፊያ በቢሾፍቱ እየገነባች ትገኛለች ሲሉ ከጉባዔው ታዳሚዎች አድናቆት እንደተቸራቸው ተናግረዋል፡፡
ጉባዔዎቹ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሁነቶችን በስኬት የማስተናገድ አቅም እንዳላት ያሳየችበት መሆኑን ጠቁመው÷ መድረኮቹ የኢኮኖሚ እንቅስቀሴን እና የቱሪስት መዳረሻን ከማስፋት አንጻር ጉልህ ሚና እንዳላቸው አብራርተዋል፡፡
በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ከ26 በላይ የሀገራት መሪዎች እና ልዑካቸው መሳተፋቸው ተመላክቷል፡፡
በመላኩ ገድፍ