ከምርጫ ስራዎች ጎን ለጎን የልማት ስራዎች በትጋት ይከናወናሉ – አቶ ጥላሁን ከበደ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ከምርጫ ስራዎች ጎን ለጎን መደበኛ የልማት ስራዎችን በትጋት እና በፅናት በማከናወን ለላቀ ውጤት ርብርብ ይደረጋል አሉ።
የክልሉ መንግሥት፣ የማዕከል እንዲሁም የ12ቱ ዞኖች እና የሶስቱ ሪጂዮ ፖሊሲ ከተሞች አስተባባሪ አካላት የተሳተፉበት የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የፓርቲና መንግሥት ስራዎች አፈፃፀም ግምገማና ምዘና መድረክ እየተካሄደ ነው።
መድረኩ በፓርቲ እና በመንግሥት የተከናወኑ ተግባራትን በመፈተሽ የተመዘገቡ ጥንካሬዎችን ለማስፋት፣ ተሞክሮዎችን ለመቀመር እንዲሁም የታዩ ድክመቶችን ለማረም እና አመራሩን ለቀጣይ ተልዕኮ ለማዘጋጀት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
አቶ ጥላሁን ከበደ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ በመደበኛና በንቅናቄ የሚመሩ ተግባራትን በመለየትና ከስልጠና ጋር በማዋሃድ ወደ ተግባር መገባቱን አስታውሰዋል።
የተገኙ ውጤቶችን በመፈተሽ በጥንካሬ የተለዩትን ይበልጥ ለማጠናከር እና ጉድለት የታየባቸውን ለማረም መድረኩ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ በአመራሩ መካከል የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት እንደሚፈጥርም አመልክተዋል።
ዓመቱ ለምርጫ ዝግጅት የሚደረግበት እና እንደ ፓርቲ ተወዳድሮ ለማሸነፍ የምንሰራበት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በበለጠ ትጋትና ፅናት መስራት ይገባናል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ለፋና ዲጂታል ገልጿል።
ከምርጫ ስራዎች ጎን ለጎን መደበኛ የልማት ስራዎችን በትጋት እና በፅናት በማከናወን ለላቀ ውጤት ርብርብ ይደረጋል ነው ያሉት።
አመራሩ ለወቅታዊ የፓርቲና መንግሥት ተልዕኮ ራሱን በማዘጋጀት ተልዕኮውን በብቃት መፈጸም እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ገ/መስቀል ጫላ በበኩላቸው ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ በማድረግና ሀገረ መንግሥቱን በማፅናት በኩል የተከናወኑ ስራዎች ላይ ጥልቅ ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ክልሉ ህብረ ብሔራዊ ክልል መሆኑን ጠቅሰው፤ አመራሩ በላቀ የመፈፀም አቅም ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍሎች ለማገልገል መንቀሳቀስ እንዳለበት አመልክተዋል።