ኢትዮጵያ ከየት ወደ የት?
የአንድ ሀገር የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጉዞ ስኬታማ የሚሆነው ካለፈችበት ታሪክ ትምህርት ሲቀሰም፣ የወደፊት መዳረሻዋ በግልጽ ሲቀመጥ እና መዳረሻው ላይ ለመድረስ የሚያስችል ቁልጭ ያለ እሳቤ ሲቀረጽና ሲተገበር ብቻ ነው።
በዚህ ረገድ የመደመር እሳቤ፣ የኢትዮጵያን ዘመናዊ የለውጥ ጉዞ ፍልስፍና በዝርዝር አስቀምጧል።
ይህ እሳቤ ኢትዮጵያ ካለፈችበት ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስብራት ተነሥታ፣ ወደፊት ልትደርስበት ወደምታልመው ሁለንተናዊ ብልጽግና የምታደርገውን ታሪካዊ ሽግግር ተንትኗል።
የመደመር እሳቤ የኢትዮጵያን ስብራቶች መነሻ ሲተነትን ሀገሪቱ በሦስት ዋና ዋና ችግሮች ውስጥ ስትማስን እንደነበር ያስረዳል።
አንደኛው ከዜሮ ድምር የፖለቲካ ባህል መውጣት ያለመቻል ነው፡፡
ባለፉት ሥርዓቶች የነበረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ አንዱ ሲያሸንፍ ሌላው የሚጠፋበት፣ የኔ ሐሳብ ብቻ ካልገዛ በሚል መጠፋፋት ላይ የተመሠረተ ነበር። ይህም ልዩነቶችን እንደ ውበትና አቅም ከማየት ይልቅ፣ የፖለቲካ ክፍፍልን በማስፋት ዜጎች ተከፋፍለው እንዲኖሩ አድርጓል።
ሁለተኛው የባዕድ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቅጂዎች አዘሩሪት ነበር፡፡ መደመር በዚህ ረገድ ያደረገው ሀገሪቷን ወደ ርዕዮተ ኢትዮጵያ እሳቤ መመለስ ነው፡፡ የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ፣ ባህልና ታሪክ ያላገናዘቡ ከውጭ የተቀዱ ርዕዮተ-ዓለሞችን በሀገሪቱ ላይ በግድ ለመጫን መሞከር ሰፊ የማኅበረሰብ ስብራት ፈጥሯል። ይህም ሀገር-በቀል ዕውቀቶችና ፀጋዎች እንዳይለሙ አድርጓል።
ሦስተኛው ከድህነት እና ከእጦት አዙሪት ያለመላቀቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊ የሰው ኃይል፣ የተፈጥሮ ሀብት እና የባህል ፀጋዎች ያሏት ቢሆንም፣ አቅሟ ሳይቀናጅና ሳይደመር በመቆየቱ ምክንያት ለዘመናት በድህነትና ጥገኝነት ማጥ ውስጥ እንድትቆይ አድርጓታል።
ይህንን ለመቀየር የመደመር መንግሥት ሦስት አበይት ቁልፍ የአሠራር ስልቶችን ተከትሏል፡፡
አንደኛው ያለፉትን ስኬቶች ማስቀጠል ነው፡፡ በዚህም ካለፉት ሥርዓቶች የተገኙ መልካም አፈጻጸሞችን መጠገን እና የማስቀጠል ስልትን መርጧል።
ሌላኛው ስህተቶችን ማረም ሲሆን፣ ይህም በሕግ የበላይነት፣ በዴሞክራሲ እጦት እና በኢኮኖሚ መዋቅር ላይ የታዩ ስህተቶችን ማረም አስችሏል፡፡
ሦስተኛው ስልትና መንገድ አዳዲስ ፈጠራዎችን ማምጣትን ያካትታል፡፡ በዚህ እሳቤ እንደ ዲጂታል ኢኮኖሚ፣ የኮሪደርና የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት፣ እንዲሁም እንደ አረንጓዴ አሻራ ያሉ አዳዲስ ሀገራዊ የፈጠራ ሥራዎች ተተግብረዋል፡፡
የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያን በ2040 በዓለም መድረክ ስሟ በክብር የሚጠራ ታላቅ አፍሪካዊት ኃይል ለማድረግ አልሟል።
በዚህም ኢትዮጵያን ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና እና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት፣ ወደ አካታች እና የመግባባት ዴሞክራሲ እንዲሁም ወደ ዓለም አርዓያነት ይወስዳል፡፡
ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን እንድትች፣ ከውጭ ጥገኝነት የሌለባት እና የኢኮኖሚ ነፃነቷ የተረጋገጠ ሀገር እንድትሆን በሁሉም ዘርፍ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡
ይህም የገጠሩን ሕይወት መለወጥና ከተሞችን ማዘመንን ተያይዞታል።
በሌላ መልኩ ዜጎች በትንንሽ አጀንዳዎች ሳይከፋፈሉ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ፤ በሐሳብ የበላይነት እና በትብብር መርህ ሥር የሚሰባሰቡባት፣ የሰብዓዊ መብት የተከበረባት ሀገር እንድትሆን እየሠራ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የሌሎችን የውጭ ሞዴል በጭፍን የምትቀዳ ሳትይሆን፣ የራሷን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሞዴል ፈጥራ ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ እንድትሆን የማድረግ ጥረቱ ቀጥሏል፡፡
በዚህ ጉዞ ውስጥ የመንግሥት ሚና የሁሉን አድራጊነት ሚና አይደለም። የሕዝብን አቅምና ፀጋ አስተባብሮ ወደ አንድ የብልጽግና መንገድ ማትመም ነው፡፡
በአጠቃላይ፣ ኢትዮጵያ በመደመር መንግሥት የምታደርገው ጉዞ ካለፈው ዘመን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ስብራት ተነሥቶ፣ የጋራ አቅምን በመደመር፣ ወደፊት የምትገነባ የተረጋጋች፣ የበለጸገች እና ሉዓላዊነቷ የተከበረ ታላቅ ሀገርን እውን ማድረግ ላይ ያተኮረ ነው።
ይህ ጉዞ የሁሉንም ዜጎች አቅም፣ ዕውቀትና ጉልበት በአንድነት ማቀናጀትን የሚጠይቅ ዘላቂ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው።