በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዕጩ ተወዳዳሪዎች የሚገዙበት የሥነ ምግባር ደንብ ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመወዳደር የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲ እና የግል ዕጩዎች የሚገዙበት እና የሚተዳደሩበት የሥነ ምግባር ደንብ ይፋ አድርጓል።
የሥነ ምግባር ደንቡ ይፋ የሆነው የተመዘገቡ ፓርቲዎች በተገኙበት ሲሆን፤ ፓርቲዎች እና የግል እጩዎች በሥነ ምግባር ደንቡ ለመገዛት የጋራ ቃልኪዳን ፈርመዋል።
ሰላማዊ የምርጫ ቅስቀሳና የምርጫ ክርክር እንዲደረግ የማስቻል ዋና ዓላማ ያለው የሥነምግባር ደንቡ፤ በምርጫ ቅስቀሳና ክርክር ወቅት ሁሉም እኩል የመወዳደሪያ ሜዳ እንዲያገኙ ያስችላል ተብሏል።
በተጨማሪም የሥነ ምግባር ደንቡ የመራጮችን ነፃነት የሚያከብር ሲሆን፤ በተለይም መራጮች በነፃነትና በፈቃዳቸው የሚፈልጉትን መምረጥ እንዲችሉ የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ የተመዘገቡ ፓርቲዎችና እጩዎች የፈረሙት ይህ የሥነምግባር ደንብ የምርጫ ስርዓቶች ተከብረው ውጤቱ ተዓማኒ እንዲሆን ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተነግሯል።
በተጨማሪም በዛሬው እለት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተመዘገቡ 48 የፖለቲካ ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ምልክታቸውን አስተዋውቀዋል።
በዓለምሰገድ አሳዬ