ሰላምን ለማጽናት ወሳኝ ሚና ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የወለጋ ዞኖች ጉብኝት
አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት በወለጋ ዞኖች ያካሄዱት ጉብኝት የአካባቢው ሰላም መሻሻሉን ያረጋገጠ ነው አሉ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ተሬቻ ባልቻ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቄለም ወለጋ፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የለማ የሙዝ እርሻ፣ የቄጦ የመስኖ መሠረተ ልማት ፕሮጀክትን፣ የቱሉ ካፒ የወርቅ ልማት ፕሮጀክትን እና የአርጆ ዲዴሳ የመስኖ ልማት ፕሮጀክትን ተመልክተዋል።
በተጨማሪም የአርጆ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ እና ማቀነባበሪያን የመረቁ ሲሆን፤ በዞኖች የተከናወኑ እና እየተከናወኑ የሚገኙ በአግሮ-ኢንደስትሪ፣ ቱሪዝም እና የገጠር ሽግግር የልማት ሥራዎች መመልከታቸው ይታወሳል።
እንዲሁም የቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ የተቀናጀ የምግብ ኢንዱስትሪ ግንባታን አስጀምረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉብኝት አስመልክቶ ከፋና ዲጂታል ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ተሬቻ ባልቻ፤ ጉብኝቱ በአካባቢው የመጣውን ሰላም የሚያጸና ነው ብለዋል።
የወለጋ ዞኖች በተሳሳተ መንገድ ገብተውበት በነበረ ችግር የአካባቢው ልማት ተጎድቶ እንደነበር ጠቅሰው፤ አሁን በመጣው ሰላም ተስፋ ሰጪ ልማት እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ይህንን ያረጋገጠ መሆኑን አንስተው፤ የታየው ልማት የአካባቢው መልካም ስም የመለሰ እንደሆነ ገልጸዋል።
ልማቱ በህዝብ እና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት እና ትብብር በማጠናከር ዘላቂ ሰላምን ይገነባል ብለዋል።
ጉብኝቱ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በመጨረስ እና በአፈጻጸም ረገድ የሚታዩ ክፍተቶችን በማረም በኩል ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡
ፕሮጀክቶቹ ግብርናን በማሳደግ፣ በስራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም ኢንቨስትመንትን በመሳብ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ እንደሆኑ አቶ ተሬቻ ተናግረዋል፡፡
የተጀመሩ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል እምቅ አቅም ያለውን የወለጋ አካባቢ ለሀገር ዕድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ከፍ ማድረግ እንደሚቻል አስገንዝበዋል።
በአያና ዴሬሳ