የኢራንን መንፈሳዊ መሪ ለሕልፈት የዳረገው የመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና ወታደራዊ ግጭት…
አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሚኒን ለሕልፈት የዳረገው የመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና ወታደራዊ ግጭት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ባለፉት ቀናት በእስራኤል፣ አሜሪካ እና ኢራን መካከል እንደ አዲስ ያገረሸው ወታደራዊ ግጭት የመካከለኛው ምስራቅ ቀጣናን ውጥረት ይበልጥ አባብሶታል፡፡
አሜሪካና እስራኤል ትናንት ጠዋት በኢራን ላይ በፈጸሙት የሚሳኤል ጥቃት የ86 ዓመቱ የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላ አሊ ኻሚኒ ሕይወታቸው አልፏል፡፡
የአያቶላህ አሊ ኻሚኒን ሕልፈት ተከትሎ ኢራን በመላ ሀገሪቱ የ40 ቀናት ብሔራዊ ሃዘን ያወጀች ሲሆን÷ አጸፋዊ ርምጃም እየወሰደች ትገኛለች፡፡
ቴህራን በአጸፋዊ ርምጃዋ እስካሁን በባህሬን፣ ኳታር፣ ኩዌትና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ የሚሳኤል ጥቃት ፈጽማለች፡፡
በዛሬው ዕለትም በእስራኤል፣ አሜሪካ እና ኢራን መካከል የሚደረገው የሚሳኤል ጥቃት ተጠናክሮ መቀጠሉ ነው የተገለጸው፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ውጥረት ይበልጥ መባባሱን ተከትሎም የቀጣናው ሀገራት የአየር ክልላቸውን ለበረራ ዝግ እያደረጉ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
👉ለፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎች የፋና ዲጂታል አድራሻዎችን ከአስተያየት መስጫ ሳጥን ያግኙ