በአቪዬሽን ሳይንስና ኤሮስፔስ ኢንጂነሪንግ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት ያለመ ስምምነት…
አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጅማ ዩኒቨርሲቲ እና ቦይንግ ኩባንያ በአቪዬሽን ሳይንስ እና ኤሮስፔስ ኢንጂነሪንግ የሰለጠኑና ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችል የትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል።
በአፍሪካ የቦይንግ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቅ የአቪዬሽን መዳረሻ ናት።
የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ታሪክ የላቀ ፍላጎት የሚንፀባረቅበት ከመሆኑም በላይ የረጅም ጊዜ ራዕይ የሰነቀ መሆኑን አንስተው÷ ሀገሪቱ ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት ረገድ እየሰራች ያለው ስራ የዚህ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።
በቅርቡ በቢሾፍቱ ግንባታ የተጀመረው ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪውን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሻግር መሆኑንም አመልክተዋል።
ስምምነቱ እያደገ ካለው የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዕድገት ጋር እኩል ለመራመድ የሚያስችል ክህሎትና ዕውቀት እንዲፈጠር በማጎልበት የአቪዬሽን ባለሙያዎች ትውልድ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጋራ ለመቅረጽ ዕድል እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጀማል አባፊጣ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ አጋርነቱ ዩኒቨርሲቲውን በአቪዬሽን ሳይንስ እና ኤሮስፔስ ምህንድስና የልህቀት ማዕከል ለማድረግ ወሳኝ ርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።
በዘርፉ በአፍሪካ የሚፈጠረው ክህሎት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ የአቪዬሽን ባለሙያዎችን ለማፍራት አቅም ይሆናልም ነው ያሉት።
በወርቅአፈራው ያለው