ማንቼስተር ሲቲ ከአርሰናል – የሳምንቱ ተጠባቂ ፍልሚያ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ33ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ማንቼስተር ሲቲ በሜዳው ኢትሃድ ምሽት 12 ሰዓት ከ30 ላይ የሊጉን መሪ አርሰናልን ያስተናግዳል፡፡
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡትን ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ የሳምንቱ ተጠባቂ መርሐ ግብር ነው፡፡
ማንቼስተር ሲቲ ከሊጉ መሪ አርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ የሚያደርገው ፍልሚያ ተጠባቂ ነው፡፡
አንድ ቀሪ ጨዋታ ያለው ማንቼስተር ሲቲ የዛሬውን ጨዋታ የሚያሸንፍ ከሆነ ከአርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሦስት ዝቅ ማድረግ ይችላል፡፡
በሊጉ ከሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች የአቻ ውጤት በኋላ ቼልሲን በማሸነፍ ወደ ድል የተመለሰው ማንቼስተር ሲቲ ተከታታይ ድሉን ለማሳካት ወደ ሜዳ የሚገባ ይሆናል፡፡
በጨዋታው ሩበን ዲያስ በጉዳት ምክንያት ለማንቼስተር ሲቲ ግልጋሎት እንደማይሰጥ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ አረጋግጠዋል፡፡
ያለፉትን ሦስት የውድድር ዓመታት በሊጉ 2ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው አርሰናል በዚህ የውድድር ዓመት ዋንጫውን ለማንሳት የሚያደርገውን ጉዞ ለማጠናከር ይፋለማል፡፡
በሊጉ ባሳለፍነው ሳምንት በቦርንማውዝ ሽንፈት ያስተናገደው አርሰናል ወደ ድል ለመመለስ የሚያደርገው ፍልሚያ ተጠባቂ ነው፡፡
የካራባኦ ካፕ ዋንጫን በማንቼስተር ሲቲ የተነጠቀውና ከኤፍ ኤ ዋንጫ ውድድር የተሰናበተው አርሰናል በቀሪ ሁለት ውድድሮች ዋንጫውን ለማሳካት ብርቱ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እንግሊዛዊው የፊት መስመር ተጫዋች ቡካዮ ሳካ ከዛሬ ምሽቱ ተጠባቂ ጨዋታ ውጪ መሆኑን አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ተናግረዋል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በሁሉም ውድድሮች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለቱም በተመሳሳይ አንድ ጊዜ ሲያሸንፉ በቀሪ ሦስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡
በሌላ የሊጉ ጨዋታዎች በተመሳሳይ ቀን 10 ሰዓት ላይ ኖቲንግሃም ፎረስት ከበርንሌይ፣ ኤቨርተን ከሊቨርፑል እንዲሁም አስቶንቪላ ከሰንደርላንድ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ