ለጎርፍና ናዳ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ለጎርፍና ናዳ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት÷ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ደጋማ ቀበሌዎች ሰሞኑን የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጉዳት ምክንያት የ30 ሰዎች ሕይወት አልፏል ፡፡
በዞኑ በቀጣይ በተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት ስጋት ሊያጋጥም እንደሚችል አመልክተዋል፡፡
ስለሆነም ወቅቱ ዝናባማ በመሆኑና መሰል አደጋዎች ሊደገሙ ስለሚችሉ በደጋማና ለናዳ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች የተሰማቸው ሐዘን ገልጸው ÷ ለቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡