አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 263 የህክምና ተማሪዎችን አስመረቀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለ54ኛ ዙር ያስተማራቸውን 263 ተማሪዎች አስመርቋል።
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የጤና አገልግሎት ጥራት፣ ተደራሽነትና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የጤና ባለሙያዎች የማይተካ ሚና አላቸው።
ተመራቂዎችም በስራቸው ሙያዊ ሥነምግባርን በመጠበቅና በርህራሄ ማገልገል እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲው ከጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር በመቀናጀት ብቁ የጤና ባለሙያዎችን በማፍራትና የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።
የዘንድሮ ተመራቂዎች 98 በመቶ የሚሆኑት የመውጫ ፈተና ማለፋቸው የዩኒቨርሲቲውን የትምህርት ጥራትና ስኬት የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ 44 የፋርማሲ ተማሪዎችን ጨምሮ ለ7ኛ ጊዜ በአራት ኮሌጆች በቅድመ መደበኛና በተከታታይ የትምህርት መርሐግብር ያሰለጠናቸውን 146 ተማሪዎች አስመርቋል።
የደቡብ ምዕራበ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አልማው ዘውዴ በምረቃ ስነስርዓቱ ባደረጉት ንግግር፥ በዕለቱ በጤና መስክና በሌሎች ዘርፎች የተመረቁ ተማሪዎች ዜጎቻቸውን በኃላፊነት እንዲያገለግሉ አደራ ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ደገላ ኤርጌኖ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ በመደበኛ ፕሮግራም እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶችን በተከታታይ መርሐግብሮችም ለማሳካት ይሰራል ነው ያሉት።
በፍሬው ዓለማየሁ