በጋሞ ዞን በተከሰተው የመሬት ናዳ የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት ርብርብ እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች በተከሰተው የመሬት ናዳ የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምሴ አድማሱ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ፥ በዞኑ የካቲት 30 እና መጋቢት 1 ቀን 2018 ዓ.ም የጣለው ከባድ የጎርፍ እና የመሬት ናዳ አደጋዎችን አስከትሏል።
በአደጋውም ጋጮ ባባ፣ ቦንኬ እና ካምባ ዙሪያ ወረዳዎች እንዲሁም በሌሎች የዞኑ አከባቢዎች በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል፡፡
በተለይ አደጋው ከፍተኛ ጉዳት ባደረሰበት ጋጮ ባባ ወረዳ ማዜ ዶይሳ ቀበሌ ቀደም ብሎ በተከሰተው ናዳ የሞቱትን ሰዎች ለማውጣት ርብርብ እያደረጉ የነበሩ 125 ሰዎች በድጋሚ የጉዳቱ ሰለባ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አደጋው ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ የነፍስ አድን ስራ እና የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው፥ እስከ ትናንትናው ዕለት 81 አስክሬን ማውጣት መቻሉን ጠቁመዋል።
የአደጋ ጊዜ ምላሹ በአካባቢው መልክአ ምድር አቀማመጥ የተነሳ እየተስተጓጐለ ቢሆንም በመላው ኢትዮጵያውያን ትብብር አስፈላጊው ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
ለተደረገውን የነፍስ አድን ስራ ምስጋና ያቀረቡት ዋና አስተዳዳሪው፤ የተለያዩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ያደረጉት ድጋፍ ለተጎጂዎች እየደረሰ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ኮሚቴ ተዋቅሮ ከዞኑ፣ ከክልሉ እና ከፌዴራል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያውያን እያደረጉ ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመለሰ ታደለ