በአማራ ክልል በሴቶችና ህፃናት ላይ የተፈፀሙ ከ200 በላይ ወንጀሎች የፍርድ ውሳኔ አገኙ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ባለፉት ስድስት ወራት በሴቶች እና ህፃናት ላይ የተፈፀሙ ከ200 በላይ ወንጀሎች የፍርድ ውሳኔ አግኝተዋል አለ፡፡
ቢሮው በጎንደር ክላስተር ባሉ ወረዳዎች ለሚገኙ ዳኞች፣ ዐቃብያነ ሕግ እና ሌሎች ባለደርሻዎች በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ የኃይል ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችል ስልጠና መስጠት ጀምሯል፡፡
በስልጠና በመድረኩ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ወንዳቸው ሰራው÷ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፀጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል ከአጋር ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በሴቶችና ህፃናት ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ አጥፊዎች ላይ ተመጣጣኝ የቅጣት ውሳኔ እንዲሰጥ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ባለፉት ስድስት ወራት ጥቃት በፈፀሙ ከ200 በላይ ግለሰቦች ላይ እስከ 25 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት የቅጣት ውሳኔ ተላልፏል ነው ያሉት።
የተጎጂዎችን የንብረት መብት ለማስከበር በተከናወኑ ተግባራት በዚህ ዓመት በ422 ሚሊየን ብር የንብረት ክርክር በማድረግ ለባለመብቶች የፍትህ ተቋማት ድምፅ መሆን መቻላቸውን ገልፀዋል።
በክልሉ ፆታዊ ጥቃትን በመከላከል እና ጥቃት ከደረሰም አጥፊዎች በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ የሚከናወነውን አበረታች ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸው፤ የፍትህ ተቋማትም በትኩረት እንዲሰሩበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ለማስከበር የህግ ማሻሻያ ስራዎች በስፋት እየተሰሩ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በምናለ አየነው