Fana: At a Speed of Life!

ተፈጥሮ የሰጠችንን ጸጋ ማወቅና መገንዘብ አለብን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተፈጥሮ የሰጠችንን ጸጋ ማወቅ፣ ማንበብ እና መገንዘብ አለብን አሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገበታ ለትውልድ ውጥን በአፋር ክልል የተገነባውን ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ በትናንትናው ዕለት መርቀው ከፍተዋል፡፡

አፋር በተፈጥሮ በእጅጉ የታደለ አካባቢ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ምድሩ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡም ሀገሩን የሚወድ፣ ብርቱና ትጉህ መሆኑን አውስተዋል፡፡

በዚህ ውብ ክልል መጠነኛ ኢንቨስትመንት እየሰራን፣ መጠነኛ ላብ እያፈሰሰን ወርቁን ለማፈስ የሚያስችል ዕድል ለልጆቻችን መስጠት እንችላለን ነው ያሉት፡፡

አፋሮች ስለ ሥራ፣ ስላለመዘናጋት እና ስለ ብርታት ብዙ እንደሚናገሩ ጠቅሰው፥ ዕድል ያንቀላፉ ሰዎችን አትቀሰቅስም የሚል በአፋር የሚታወቅ ጥሩ አባባል መኖሩን ገልጸዋል፡፡

አፋር ትልቅ ዕድል ያለበት ክልል እንደመሆኑ በእኛ ማንቀላፋት እንጂ ይህ ቦታ መሰራት የነበረበት ከዛሬ 50 እና 60 ዓመታት በፊት ነበር ብለዋል፡፡

የተፈጥሮ ጸጋን ባለማወቅ ይህ ውብ ቦታ ሳይታይ መቆየቱን ገልጸው፥ አፋር ገና እንዳልተነካ በመገንዘብ ይህን መነሻና ጅማሮ ይበልጥ አግዝፈን ለማስቀጠል እንተጋለን ነው ያሉት፡፡

ለውጥ ተዘጋጅተው ለሚጠብቁ ሰዎች የሚበረከት ጸጋ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ሰው ለለውጥና ለዕድገት ራሱን ካዘጋጀ ከትናንሽ ነገሮች ውስጥ በርከት ያለ ጸጋ ለማውጣት እንደሚታደል አስረድተዋል፡፡

የመለወጥ መሻት በውስጡ ከሌለ ግን ምንም ያህል ውብ ስጦታ በአካባቢው ቢኖርም ያንን ወደ ሃብት ለመቀየር እንደማይተጋ ገልጸዋል፡፡

ጊዜን ማወቅና መጠቀም የሁላችንም ትጥቅ ልብስ መሆን እንዳለበት አንስተው፥ አፋሮች “ላብ ወርቅ ያስገኛል ስንፍና ግን አቧራ ያስታቅፋል” የሚል አባባል እንዳላቸው አስታውሰዋል፡፡

በመካከለኛው ምስራቅ በተፈጠረው ችግር ነዳጅ እና የአፈር ማዳበሪያን የመሳሰሉ አስፈላጊ ግብዓቶች አደጋ እንደደረሰባቸው ጠቁመዋል፡፡

በዓለም ላይ የመጣው ነገር ከባድ ቢሆንም ፈጣሪ በሰጠን ዝናብ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ቢያንስ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት በበልግ ማረስ ከቻልን ብዙ ነገሮችን መሸፈን እንችላለን ሲሉ አመልክተዋል፡፡

በመካከለኛው ምስራቅ በተፈጠረው ችግር ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሚቸገሩ ሰዎች ጭምር ለመድረስ ዕድል እንደሚሰጥም አብራርተዋል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.