Fana: At a Speed of Life!

የዲጂታል ፋይናንስ ማጭበርበርን ለመግታት …

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የዲጂታል ፋይናንስ ማጭበርበርን ለመግታት በትኩረት እየተሰራ ነው አለ፡፡

አስተዳደሩ “ደህንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ፋይናንስ ለሀገራዊ እድገት” በሚል መሪ ቃል ከተለያዩ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት÷ የቴክኖሎጂ አድማስ መስፋት ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ጉልህ ሚናን እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም ቀልጣፋና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት መስጠት መቻሉን ተናግረዋል።

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ውጤታማ የነበረውንና በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 በስትራቴጂነት የተቀመጠውን ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የዲጂታል ኢኮኖሚ ማዕከል የማድረግ ትልም እንዲሳካ ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የቴክኖሎጂ መስፋፋት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ያሉት ቢሆንም የዲጂታል ፋይናንስ ማጨበርበር የመላው ዓለም ስጋት ሆኖ መዝለቁን ጠቁመዋል፡፡

ችግሩን ለመከላከል ተቋማት ተቀራርበው እና ተናበው መስራት እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት፡፡

የፍትህ ሚኒስትር ሀና አርዓያስላሴ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በዲጂታል ዘርፍ ያስመዘገበችው ስኬት የሚደነቅ መሆኑን ገልፀዋል።

ዘርፉ ውስብስብ ተግዳሮቶች ያሉት መሆኑን ጠቅሰው÷ የዲጂታል ፋይናንስ ማጭበርበር ድንበር ተሻጋሪ የወንጀል አይነት በመሆኑ የሀገርና የዓለም ደህንነትና ሉዓላዊነት ላይ ስጋት የጣለ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በመሆኑም ችግሩን የመከላከል አቅም ለመፍጠር ተቋማዊ አቅምን ማጠናከር እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥተው፤ እንደ ሀገር ተጠያቂነትን ማስፈን የሚያስችሉ ርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በታምራት ደለሊ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.