የለውጡ መንግሥት አንዱ ምሰሶ የሆነው ሕብረ ብሔራዊ አንድነት…
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ወደ ስልጣን የመጣው የለውጡ መንግሥት ባለፉት ስምንት ዓመታት የኢትዮጵያን ሕብረ ብሔራዊ አንድነት አንዱ የሀገሪቱ ምሰሶ በማድረግ የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል።
በዚህም ሀገራዊ መግባባት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት መሰረት መሆኑንና የወል ትርክቶች ተሰናስለውና ተዋኅደው ሲፈሱ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት እንደሚገነባ በማመን በትኩረት ሰርቷል።
በየዓመቱ በሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓልን የሕዝቦችን አንድነት በሚያጠናክሩ ርዕሰ ጉዳች ላይ ትኩረት በመስጠት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጎሉ ስራዎችን መስራት ተችሏል።
መንግሥት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከርና ለአሰባሳቢ ትርክት ግንባታ በቁርጠኝነት በመስራቱም በኢትዮጵያ ለዘመናት ሥር ሰደው የቆዩና ያለመግባባት መነሻ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት በርካታ የሪፎርም ርምጃዎች ተወስደዋል፡፡
በዚህም ፖለቲካዊ ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ በመስራት የተፈጸሙ በደሎችን በእርቅ፣ በይቅርታ እና በፍትሕ ለመሻገር የተለያዩ ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል።
በሀገራዊ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ሕዝብ በአጀንዳዎቹ ላይ ምክክር አድርጎ መፍትሔ የሚያቀርብበት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማቋቋም የተለያዩ አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ሥራዎች እየተከናወነ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።
የለውጡ መንግሥት ኢትዮጵያዊ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጎለብት ልዩ ትኩረት በመስጠትም ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ትስስርን የማጠናከር ሥራዎችን በቁርጠኝነት እየሰራ ነው፡፡
በዚህም ሕብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከርና የሀገረ መንግሥት ግንባታ እንዲሳካ ነጣጣይ ትርክቶች ተሸንፈው አስተሣሣሪ ትርክቶች የበላይነት ማግኘት እንዳለባቸው ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ አየሰራ ይገኛል።
በአድማሱ አራጋው