አቶ አህመድ ሺዴ ከእስያ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ከእስያ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ፕሬዚዳንት ጋር በኢትዮጵያ እና በባንኩ መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ በኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት ስራዎችን ማስፋፋት በሚቻልባቸው ጉዳዮች በተለይም የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማሪፊያ ፕሮጀክትን በፋይናንስ ለመደገፍ የሚያስችል ምክክር ተደርጓል፡፡
አቶ አህመድ ሺዴ በዚህ ወቅት÷ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማሪፊያ ፕሮጀክት የኢትዮጵያን ቀጣናዊ የአቪዬሽን ማዕከልነት ሚና ለማሳደግ እና የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አብራርተዋል፡፡
የግሉ ዘርፍ በመሰረተ ልማት ግንባታ ያለውን ተሳትፎ ለማጠናከር የእስያ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች የግሉን ዘርፍ ለማጠናከር የሚውል ፋይናንስ በማሰባሰብ ረገድ ያለውን ትብብር ለማጠናከር የሚያስችሉ ዕድሎችን በተመለከተም ምክክር አድርገዋል፡፡
በተጨማሪም በውይይቱ በኢትዮጵያ ዘላቂ የመሰረተ ልማት ዝርጋታን ለማጠናከርና የግሉን ዘርፍ ዕድገት ለመደገፍ በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ እንደሆኑ ማረጋገጣቸውን ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ አመላክቷል፡፡