በአማራ ክልል ከ8 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማሰራጨት…
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ከ8 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማሰራጨት ታቅዷል አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ፡፡
በቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አንተነህ ሰውአገኝ ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት÷ በክልሉ የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
በክልሉ ለመኸር እርሻ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ አስፈላጊውን የግብርና ግብዓቶች በወቅቱ ለማሰራጨት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለ2018/19 የምርት ዘመን ከታቀደው 8 ሚሊየን 640 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ እስካሁን 2 ነጥብ 96 ሚሊየን ኩንታሉ በክልሉ በሚገኙ ዩኒየኖች መሰራጨቱን አመልክተዋል፡፡
ከዚህም ውስጥ 1 ሚሊየን 439 ሺህ 390 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለሕብረት ስራ ማሕበራት መከፋፈሉንና 799 ሺህ 706 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለምርት ዘመኑ የሚቀርበው ማዳበሪያ ያለምንም መስተጓጎል ስርጭቱ የተሳለጠ እንዲሆን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡።
አርሶ አደሮች ማሳቸውን በማለስለስ ለዘር ማዘጋጀት፣ የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ መውሰድና የግብርና ባለሙያዎች የሚሰጧቸውን ምክረ ሐሳብ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ