ፈተናዎችን ወደ እድል – የለውጡ መንግሥት መገለጫ …
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ ለውጡ እውን ከሆነበት 2010 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ያጋጠሙ በርካታ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር ስኬቶች ተመዝግበዋል።
በለውጡ ዓመታት መንግሥትን ከገጠሙት ፈተናዎች መካከል ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር የተገናኙ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች፣ የሰሜኑ ጦርነት እና ኮቪድ-19 ይጠቀሳሉ።
በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተላቸው ድርቅ፣ የመሬት መንሸራተት፣ ጎርፍ አደጋዎች እና ሌሎች ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች የለውጡን መንግሥት በእጅጉ ፈትነውታል፡፡
ከህዳሴ ግድብ ጋር በተገናኘ የነበረውን ውጫዊ ጫናን በመቋቋም እንዲሁም የፕሮጀክቱን ብልሹ አፈጻጸም በማስተካከል ለፍጻሜ በማብቃት ሊመረቅ ችሏል።
ግብጽ ለመከተል በፈለገችው ፍትሐዊ ያልሆነ የውሃ አጠቃቀም አስተሳሰብ የተነሳ የግድቡ ግንባታ ሂደት እንዲደነቃቀፍ እና ዲፕሎማሲያዊ ጫናው እንዲበረታ ያልተጓዘችበት መንገድ አልነበረም።
ኢትዮጵያ ለዚህ ፈተና እጅ ባለመስጠት ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም አቋሟን በጽኑ በመያዝ ግድቡን ከዳር በማድረስ የቀጣናው የኃይል ማስተሳሰሪያ ገመድ ልታደርገው በመብቃት ታሪካዊ ድል አስመዝግባለች።
ግድቡ ቀጣናዊ ትስስርን በማጎልበት ረገድ የላቀ ሚና እንደሚጫወት በግድቡ የምረቃ መርሐ ግብር ላይ የታደሙ የቀጣናው ሀገራት መሪዎች ምስክርነት መስጠታቸው ይታወቃል።
ለፕሮጀክቱ መጓተት ማነቆ የነበሩ ብልሹ አሰራሮችን በማስወገድ እንዲሁም ግንባታውን ለማፋጠን የለውጡ መንግሥት የአመራሮችና የኮንትራክተር ለውጥ በማድረግ አስደናቂ አፈጻጸምን አስመልክቷል፡፡
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተከናወኑ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በአጭር ጊዜ ለውጥ ለማምጣት ያስቻሉ ሲሆን የኢትዮጵያን የእዳ ጫና መቀነስ፣ የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ፣ የሀገር ውስጥ ገቢንና የወጪ ንግድን መጨመር ተችሏል፡፡
ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ጫና የሚፈጥሩ ሁኔታዎች ቢከሰቱም ችግሮችን ተቋቁሞ ተከታታይ እድገት ያስመዘገበ ኢኮኖሚ ተገንብቷል።
ከሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ጋር ተያይዞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የዋጋ ንረትን ለመቋቋም የለውጡ መንግስት በሀገር ውስጥ ምርታማነትን በመጨመር፣ የውጪ ንግድን ይበልጥ በማሻሻልና የሀገር ውስጥ ገቢን ከፍ በማድረግ በኢኮኖሚው ላይ የተከሰቱ ፈተናዎችን ተቋቁሞ አልፏል፡፡
በሀገር ውስጥ ግጭት ጠማቂዎችን አደብ ከማስያዝ ጎን ለጎን የከተሞችን ገጽታ የቀየረው የኮሪደር ልማት ስራ፣ የበጋ መስኖ ስራዎች እና ሌሎችም በርካታ ስኬቶች በለውጡ መንግስት ተመዝግበዋል፡፡
በአቤል ነዋይ